የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሂደት በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁ የሚያስመሰግን ነው ... የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

48

ኢዜአ፤ ህዳር 12/2012 የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሂደት በሰላም መጠናቀቁ የሚያስመሰግን መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ።

በኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የምርጫ ታዛቢ ቡድን የህዝበ ውሳኔውን ሂደት መከታተሉ ተገልጿል።

የታዛቢ ቡድኑ ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው፤ አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ አለመረጋጋት እንጻርና በተጣበበ ጊዜ ገደብ ውስጥ የሕዝበ ውሳኔው ሂደት በሰላም መጠናቀቁን አንድቋል።

በሪፖርቱ እንደተገለጸው፤ በሲዳማ ዞን በሚገኙ በአምስት የከተማ አስተዳደርና በ15 ወረዳዎች የድምጽ አሰጣጡን ሂደት መታዘብ ተችሏል።

በተመለከታቸው አካባቢዎች በአብዛኛው ድምጽ የሚሰጠው ማህበረሰብ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታና በትዕግስት ማከናወኑ የሚመሰገን መሆኑን ገልጿል።

ለዚህም ስኬታማነት የፌዴራልና ክልሉ መንግስት እንዲሁም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጋራ በመቀናጀት መስራት በመቻላቸው እንደሆነና ህዝቡም ወረፋውን በትግስት በመጠበቅ ድምጹን በመስጠቱ ታዛቢ ቡድኑ ምስጋናውን አቅርቧል።

በምርጫ ወቅትም የሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደርን የሚፈቅድ የሻፌታ ምልክት በስፋት ለመራጮች ገለጻ ሲደረግ  እንደነበር ጠቁሟል።

ሲዳማ ዞን ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር የመቆየት የሚደግፈው ምልክት ጎጆ ደግሞ ምንም ጫና ባይደረግበትም በምርጫ ወቅት ገለጻ ለመስጠት በመጠኑ ፍርሃት እንደነበር በሪፖርቱ ይፋ ሁኗል።

2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ ለምርጫ መመዝገቡን የጠቆመው ቡድኑ በተለይ የመሰብሰብ፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶች መከበራቸውን ገልጿል።

ይሁን እንጂ በምርጫው አሰጣጥ ሂደት በአንዳንድ የምርጫ አካባቢዎች የተወሰኑ ክፍተቶች እንደነበሩ ሳይጠቅስ አላለፈም ሪፖርቱ።

የተዘጋጁት የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ከመራጩ ቁጥር ጋር አለመጣጣም፣ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስራቸውን በትክክል አለመወጣትና የምርጫ ታዛቢዎች  በትክክል በቦታው አለመገኘት ችግሮች መታየታቸውን ተጠቁሟል።

እንዲሁም ከምርጫው ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች በስፍራው መገኘት፣ ምስጢር መጠበቅ አለመከበር፣ በድምጽ አሰጣጡ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ የሚሰጥ የሰው ሃይል አለመሟላትና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በአንዳንድ ቦታዎች አለመገኘት መታየቱን ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም