በዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል ነጻ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

54
ሰመራ (ኢዜአ) ህዳር 12 ቀን 2012ዓ.ም በአፋር ክልል የዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከመጣ የዓይን ሕክምና ቡድን ጋር በመተባበር ለሕብረተሰቡ የነጻ ዓይን ሕክምና በመስጠት ላይ መሆኑን አስታወቀ። የነጻ ሕክምና አገልግሎቱ ለ5 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን 500 ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። የሕክምና ቡድኑ አስተባባሪ አቶ በላይ በለጠ እንዳሉት በነጻ አገልግሎቱ ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ ለሚከሰተው የዓይን ሞራ ግርዶሽና ሌሎች የዓይን ሕመሞች ሕክምና ይሰጣል። ሕክምናው ከትናንት ጀምሮ እየተሰጠ ያለው የዓይን ስፔሻሊስ ኃኪሞች የሌሉባቸው አካባቢዎችን ታሳቢ በማድረግ መሆኑንም አመልክተዋል። በዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡና የዓይን ሞራ ችግር ላለባቸው ታካሚዎች የአይን ሞራ ገፈፋ ሕክምና እየተሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል። አቶ በላይ እንዳሉት በእነዚህ ቀናት የሕክምና ቡድኑ 500 ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። በቀጣይም በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መሰል የሕክም አገልግሎት በነጻ ለመስጠት መታቀዱን አመልክተዋል። ከተላላክ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ሳልሃ መሀመድ አንድ አይናቸው ከ7 ዓመት በፊት ጀምሮ በዓይን ሞራ ቢሸፈንም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለመተካም ሳይችሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ዓይናቸው በመታመሙ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽዕኖ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው በተለይ ማታ ማታ ያለሰዎች እርዳታ መንቀሳቀስ ተስኗቸው እንደነበር አመልክተዋል። በዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል በተደረገላቸው የዓይን ሞራ ገፈፋ ዓይናቸው ዳግም ማየት በመቻሉ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከአይሳኢታ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ኤይሻ ከሎይታ በበኩላቸው እንደገለጹት ከ5 ዓመት በፊት የጀመራቸው የዓይን ሕመም ከቅርቡ ግዜ ወዲህ ተባብሶባቸው ቆይቷል። "ለሕክምና ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ወደመቀሌ ከተ ብሄድም ለአገልግሎቱ ረጅም ቀጠሮ ስለተሰጠኝ ሳልታከም ቀርቺያለሁ" ብለዋል። ባጋጠማቸው የገንዘብ ችግር በቀጠሮ ቀን ተመልሰው ባለመሄዳቸው ተስፋ ቆርጠው እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት ባገኙት ነጻ ሕክምና እይታቸው ተሻሽሎ የመኖር ተስፋቸው መለምለሙን ገልጸዋል። ከዱብቲ ወረዳ የመጡት አቶ ሰኢድ አህመድ በበኩላቸው እንዳሉት ከ3 ዓመት በፊት በአንድ ዓይናቸው ላይ በተፈጠረ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በመንግስት ሥራቸው ላይ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ተቸግረው ነበር። በአሁኑ ወቅት በዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል በተሰጣቸው ነጻ የቀዶ ሕክምን አገልግሎት ብርሃናቸው በመመለሱ በተሰማሩበት የመንግስት ሥራ ኃላፊነታቸውን በተሻለ ለመወጣት መቻላቸውን አመልክተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም