ድርጅቶች በምርት ጥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ተጠየቀ

81
ህዳር 12/2012 ድርጅቶች በሚያመርቷቸው ምርቶች ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት ከተመረጡ ስምንት የፍተሻ ላብራቶሪዎች አገልግሎት ሰጪና አራት የካሊብሬሽን ላብራቶሪ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ለአክሪዲቴሽን የሚያበቃ የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል። ድጋፍ የተደረገላቸው ተቋማት ደግሞ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ እና በምግብ ዘርፍ ላይ የካሊብሬሽንና የአክሪዲቴሽን ላብራቶሪ ሰጪ ድርጅቶች ናቸው። ሚኒስቴሩ በዚሁ ጊዜ ድርጅቶች በምርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው እሸቴ አስፋው በስምምነቱ ላይ እንዳሉት ተቋማት በምርት ሂደት ወቅት ጥራቱን ጠብቀው እንዲያመርቱ ሚኒስቴሩ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል። የሚመረቱት ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁና በጥራታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት። ፕሮጀክቱ ለግል ድርጅቶች የቴክኒክ ድጋፍ፤ ለመንግስት ተቋማት ደግሞ የመሳሪያ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ዛሬም ተመሳሳይ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ተጨማሪ ስምምነት ነው ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የተፈራረመው። የቴክኒክ ድጋፉ የስልጠና፣ የግንዛቤ ማስጨበጫና የአቅም ማጎልበት መሆኑንም ገልጸዋል። በድጋፉ የሚመረቱት ምርቶችን ጥራት ማሻሻል፣ በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው ምርት እንዲቀርብ ያስችላል ብለዋል። በዚህም ጥራት አረጋጋጭ ተቋማትን ለመደገፍና ለማበረታታት እገዛ ያደርጋል ተብሏል። ተቋማቱ ከመንግስት ድርጅቶች ጋር በመሆን ጥራት ያላቸው ምርቶችን በማምረት የአገሪቷን የውጭ ምንዛሪ የሚያሳድጉ የወጪ ምርቶችን እንዲያመርቱ ለማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን የሚያመርቱ ተቋማት በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት በማድረስ በአገር ላይ ችግር እንደሚያስከትሉም ጠቁመዋል። በአገሪቷ ከላብራቶሪ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታትም በቀጣይ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ከውጭ የሚገቡ ማንኛውም ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፤ ቁጥጥሩ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ጠቁመዋል። የጅምላ አከፋፋዮችም ለምርቶች ክምችት ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው፤ ይህን በማያደርጉ ድርጅቶች ላይ መንግስት እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም