ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በመጪው ታህሳስ ወደ ህዋ ልታመጥቅ ነው

109
ህዳር 12/2012 ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይቷን በመጪው ታህሳስ ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ አስታወቀች። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ታህሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም 12 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሳተላይቷን ወደ ህዋ ታመጥቃለች። ሚኒስትሩ ዛሬ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና ምርምር ማዕከል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሳተላይቷ ከቻይና መንግስት የጠፈር ምርምር ተቋም ጋር በመተባበር ወደ ህዋ እንደምትመጥቅ ነው ያስታወቁት። የፕሮጀክቱ ስምምነት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በ2008 ዓ.ም ከቻይና መንግስት ጋር የተደረገ  መሆኑን ያወሱት ሚኒስትሩ በ2009 ዓ.ም ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል። በፕሮጀክቱም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ኢትዮጵያዊያን መሃንዲሶች የተሳተፉበት ሲሆን ሳተላይቱ ከመጠቀ በኋላም በኢትዮጵያውያን የሚመራ መሆኑ ተገልጿል። ቻይና አገር የተሰራችውና 72 ኪሎ ግራም የምትመዝነው ሳተላይቷ በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና፣ በአየር ንብረት፣ ለውሃ፣ ለአደጋ መከላከል፣ ለደን ልማትና ለመሬት አስታደደር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደምታበረክት ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት። ታህሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ከቻይና ቤጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትወነጨፈው የኢትዮጵያ ሳተላይት ከመሬት 700 ኪሎ ሜትር ርቃ እንደምትቀመጥም ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሳተላይቷ ወደ ህዋ ከመጠቀች በኋላም ለሳተላይቷ ትዕዛዝ ለመስጠት፣ ለመከታተል እንዲሁም ከሳተላይቷ የሚገኘውን መረጃ ለመቀበል የሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ ማዕከል በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና ምርምር ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ መጠናቀቁም አብራርተዋል። በቀጣይነትም አገሪቷ የራሷ የኮሙኒኬሽንና የብሮድካስት ሳተላይት እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለሳተላይቱ የወጣውን ወጪ በተመለከተ 6 ሚሊዮን ዶላር ከቻይና መንግስት በእርዳታ የተሰጠ ሲሆን የባለሙያ ስልጠና ወጪና በእንጦጦ የተገነባውን ማዕከል ወጪን ጨምሮ የኢትዮጵያ ድርሻ ደግሞ ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሏል። የሳተላይቷ ምልከታ የኢትዮጵያ፣ በምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ አካባቢዎች ሆኖ በሰሜንና ደቡብ በ80 ዲግሪ ላቲቲውድ ላይ እንደሚሆንም ተገልጿል። ይህም የኢትዮጵያ መንግስት ለሳተላይት መረጃ ሲያወጣ የነበረውን ወጪ ከመቀነሱም ባሻገር አገሪቷ በዘርፉ ያላትን አቅምና ልምድ እንደሚያሳድግላትም ተገልጿል። ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በምታመጥቅበት ወቅት ከቻይና ቤጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው ማስወንጨፊያ ሥፍራም ሆነ ከኢትዮጵያ መቆጣጠሪያ ጣቢያም የቴሌቭዠን ቀጥታ ስርጭት እንደሚኖርም ከወዲሁ ይጠበቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም