ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለፖሊሲ ማሻሻያ ግብዓት የሚሆኑ ግኝቶችን ይፋ አደረገ

106
ኢዜአ ህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለፖሊሲ ማሻሻያ ግብዓት የሚሆኑ ግኝቶን ይፋ አደረገ። ሚኒስቴሩ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የንግድና ልማት ድርጅት (UNCTAD) ጋር በመተባበር ያስጠናውን ሪፖርት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ ይፋ አድርጓል። በሳይንስ መስክ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲተገበር የቆየውን ፖሊሲ የአፈጻጸም ክፍተት የሚቃኝ ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል። ጥናቱ የቀድሞው ፖሊሲ ምን ችግሮች አሉበት?፣ ምን ያህል ያሰራል?፣ በቀጣይ አገሪቷ ከዘርፉ በተገቢው መንገድ እንድትጠቀም ምን ሊደረግ ይገባል የሚለውን የያዘ ሲሆን ከ150 በላይ ተቋማት እንደተሳተፉበት ተጠቅሷል። በዚህም መሰረት ግኝቶችን መሰረት በማድረግ የፖሊሲ ማሻሻያ እንደሚደረግ ተገልጿል። ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፖሊሲውን ማሻሻል ያስፈለገው አገሪቷ የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ከዓለም አገሮች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ ነው። በተለይም ላለፉት ዓመታት የሳይንስ ባለሙያዎችን ለማብዛት 70/30 የትምህርት ፖሊሲ ቢቀረጽም ስራ በመፍጠር ረገድ ብዙ ጉድለቶች እየተስተዋሉ በመሆኑ ይህንን ከግምት ያስገባ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በአገሪቷ የሚመረተውን ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በትኩረት ይሰራል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አባል መሆኗን ያስታወሱት ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን፤ የሚመረቱ ምርቶች በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል የማሻሻያው አካል መሆኑን ጠቁመዋል። በሚኒስቴሩ የፖሊሲ፣ ስትራቴጂና እቅድ ዳይሬክተር አቶ ደስታ አበራ በበኩላቸው ፖሊሲውን መከለስ ያስፈለገው አገር በቀል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማደረግ ነው። በቅንጅት መስራት ላይ ያሉ ክፍተቶች መራቸውን ገልጸው፤ የሰው ኃይል ሳይበቃ ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚሉ ጉዳዮች እንደሚነሱም ነናግረዋል። ዲጂታል ኢኮኖሚን ማበረታት ላይ ውስንነቶች መኖራቸውና በምርምር ስራዎች ወደ ምርትና አገልግሎት የሚቀየሩበት መንገድ አለመቀመጡ የቀድሞው ፖሊሲ ውስጥ ከነበሩ ክፍተቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል። ክለሳው እነዚህ ችግሮችን መነሻ ያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ''በጥናት የተለዩትን ግኝቶች እንደ ግብዓት በመጠቀም ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የፖሊሲ ማሻሻያ ይደረጋል'' ብለዋል። የተመድ የንግድና ልማት ድርጅት የቴክኖሎጂና ሎጂስቲክ ዘርፍ ዳይሬክተር ሻሚካ ሲሪማኔ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው መስክ እየተገበረች ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማ እንዲሆን ያልተቆጠበ እገዛ ያደርጋል። ''በተለይም የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ላይ ያሉ ጅምሮች የሚበረታቱ ናቸው'' ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በዚህም ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን እንድሚቆሙ አረጋግጠዋል። ''ፖሊሲ ማዘጋጀት የመጀመሪያው ደረጃ ሥራ ነው፤ በፖሊሲን ወደ ተግባር መቀየር ግን ዋናው ነው'' ሲሉ አመልክተዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም