ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ እንቅስቃሴ የበኩላችንን እንወጣለን - የሐረርና አካባቢው ነዋሪዎች

51
ሀረር ሰኔ 14/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እያከናወኑ ለሚገኙት የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሐረርና አካባቢው የሚኖሩ አስተያየት ሰጪዎች ገለፁ፡፡ ነዋሪዎቹ እንደገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከህዝብ ተወካይዎች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ ተከታትለዋል፡፡ ከከተማው ነዋሪዎች መካከል የአፍረን ቀሎ ሁምበና አባ ገዳ ሙሳ ሮባ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከኢትዮጵያ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ባሉት ሐገራት ላይ የልማት ትስስር እንዲኖር ለማድረግ እያደረጉ ያሉት ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ “እንደ አገርም የህዝብ ትርታን በማዳመጥ ሙስናንና የመልካም አስተዳደር ችግርን በመከላከል፣ ሰላምና ጸጥታን በማስፈን፣ አንድነትን ለማጠናከር የሚያከናውኑት ተግባር የሚበረታታ ነው'' ብለዋል። “በአገሪቱ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት ህብረተሰቡን በማወያየትና ሌሎች ተያያዢ ጥያቄዎች በሂደት እንደሚፈቱ ያስተላለፉት መልእክት በህዝቡ ዘንድ በራስ ተነሳሽነት ሰላም ለማስፈን መነቃቃትን ፈጥሯል'' ብለዋል፡፡ ወጣት ታጁ ኡመር በበኩሉ በአገሪቱ ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ እየገጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት የልማት ድርጅቶች ከፍተኛውን ድርሻ መንግስት ወስዶ ቀሪውን ባለሀብቱ የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖረው መደረጉን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ የበለጠ ግልጽ እንደሆነለት አስረድቷል፡፡ አቶ ቶፊቅ አሜ እንደሚገልጹት በኢትዮ - ኤርትራ ድንበር መካከል ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት የቀረበው ጥሪ የአካባቢውን ሰላምን ከማስፈንና ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ የመነጨ ሐሳብ በመሆኑ ሁለቱን አገራት የሚጠቅምና በአገራቱ ሰላምን የሚያሰፍን መሆኑን ተናግረዋል። “አጥፊዎችን ከጥፋት ለመመለስ እና ይቅርታና ምህረት ምን እንደሆነ የገለጹበት መንገድ እጅግ የሚበረታታና ሁሉም በአንድነት ለስኬቱ እንዲረባረብ የሚያነሳሳ በመሆኑ እኔ እረክቼበታለው'' ያሉት ደግሞ አቶ ደስታ ጥላሁን ናቸው። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እያከናወኑ የሚገኙትን አገራዊና አህጉራዊ ለውጦችን እንደሚደግፉና ለስኬታማነቱም የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም