የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ ይሆናሉ ተባለ

58
ህዳር 12/2012 የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በማምረቻው ዘርፍ ቢሳተፉ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል መኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የደቡብ ኮሪያ አቻቸውን ዩን ካንግሃዬን  በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። በዚህ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ የተካሄደው የቢዝነስ ፎረም አጋጣሚ ፈጥሯል። የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢሳተፉ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል በመኖሩ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ዶክተር አክሊሉ ጥሪ አቅርበዋል። የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዩን ካንግሃዬን በበኩላቸው የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በጤና፣ በጨርቃጨርቅና በኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት መዋዕለ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኮሪያን በጎበኙበት ወቅት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል። በጉብኝቱ ወቅት የጋራ መግባባት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት አፈጻጸማቸውን መከታተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የቢዝነስ ግንኙነት ለማጠናከርና ባለሃብቶችን ለመሳብ እንዲቻል በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረመው የተደራራቢ ቀረጥ ማስወገጃ ስምምነት በተቻለ ፍጥነት ፀድቆ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በተጨማሪም በሂደት ላይ ያለው የኢንቨስትመንት ጥበቃና ማስፋፊያ ስምምነት ቶሎ የሚፈረምበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በመጪው ዓመት የኢትዮ-ኮሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባን ለማድረግ ከወዲሁ የቅድመ-ዝግጅት ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በኢትዮጵያ ለሚሰሩ የኮሪያ ባለሀብቶች የኮሪያ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም