በዞኑ ከ5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጀ

78
ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም---በምስራቅ ጎጃም ዞን የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በተደረገ እንቅስቃሴ ከ5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ጥራቱን የጠበቀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። አርሶ አደሮች በበኩላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው መጠቀማቸው ለዘመናዊ ማዳበሪያ ያወጡት የነበረውን ወጪ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ እያለ ዳኘ እንደገለጹት የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ  በትኩረት እየተሰራ ነው። በተያዘው ዓመት ከ8 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ በተካሄደ ርብርብ ባለፉት ሁለት ወራት ከ5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ማዘጋጀት ተችሏል። ቁጥራቸው ከ200 በላይ በሚሆኑ የግብርና ማሰልጠኛ ተቋማት የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንዴት በጥራት ማዘጋጀት እንደሚቻል ለአርሶ አደሮች ስልጠና መሰጠቱንም አቶ እያለ አመልክተዋል። ባለሙያው እንዳሉት እስካሁን በበጀት ዓመቱ የተዘጋጀው ኮምፖስት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ብልጫ ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑ በግምገማ ተረጋግጧል። በማቻከል ወረዳ የኳሽባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አስረሳ ተሻገር በበኩላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) አዘጋጅተው መጠቀም ከጀመሩ አራት ዓመታት እንደሆናቸው ተናግረዋል። በእዚህም "በየዓመቱ ለዘመናዊ ማዳበሪያ ግዥ አወጣው የነበረውን እስከ 3 ሺህ ብር ወጭ ቀንሺያለሁ" ያሉት አርሶ አደሩ ሦስት ሄክታር የሚጠጋ መሬታቸው ለምነቱ እየጨመረ ምርታማነታቸው ማደጉን ገልጸዋል። ዘንድሮም ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ከአካባቢ ቁሳቁሶች ከ30 ሚትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በደጀን ወረዳ የኩራር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞኝሆዴ ዋለ በበኩላቸው " የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቼ መጠቀሜ ዘመናዊ ማዳበሪያ ፈጥኖ ሳይቀርብ ሲቀር ይፈጠር የነበረውን ጭንቀት አስቀርቶልኛል " ብለዋል። እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ምርት መስጠት አቁሞ የነበረው ሩብ ሄክታር መሬታቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ የአፈር ለምነቱ ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ምርታማነቱ በእጥፍ አድጓል። ባለፈው ግንቦትና ሰኔ ወራት የዘመናዊ ማዳበሪያ ስርጭት ሲዘገይ በራሳቸው ያዘጋጁትን የተፈጥሮ  ማዳበሪያ ተጠቅመው በወቅቱ በመዝራታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በዞኑ የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከ150 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የአርሶ አደሮች ማሳ ጥቅም ላይ መዋሉ ተመልክቷል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም