የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች መብት ለማስከበር የብዙሃን መገናኛ ድጋፍ ተጠየቀ

34
አዳማ ኢዜአ ህዳር 12 ቀን/2012… ለሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች መብት መከበር የብዙሃን መገናኛ አካላት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተከታታይ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ። የሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ለማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ ባለሞያዎችና ለሚዲያ  አካላት ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ የስልጠና መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። የሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት የሚዲያ አካላት በሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ዙሪያ የተደነገጉ ዓለም አቀፍ መብቶች እንዲከበሩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል። በተለይም የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በአካባቢያቸው ቋንቋ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መልዕክቶችን በመቅረጽና በማስረጽ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ከሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት ረገድ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዲሁም በህትመት ውጤቶች ላይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች በሚመለከቱ  ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ፖሊሲዎች፣ስትራቴጂዎችና የአሰራር ማዕቀፎች ዙርያ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህን የስልጠና መድረክ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል ። በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር፣የሚገጥማቸውን የመረጃ እጥረትና የአቅም ክፍተት ለመቅረፍና የተሳለጠ የመረጃ  ልውውጥ ሥርዓት ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። በሚኒስቴሩ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ምንያምር ይታይህ በበኩላቸው ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከል ኢትዮጵያ ያለ ዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚረዳ አዲስ ብሄራዊ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ፍኖተ ካርታው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ችግሩ በስፋት በሚፈጸምባቸው 600 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ። ፍኖተ ካርታው ለማዘጋጀት ሶስት ዓመት መውሰዱን አመልክተው ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ከግምት በማስገባት እስከ 2017 ዓ.ም ድርጊቱን ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል። ለሶስት ቀናት በተዘጋጀውና ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው በዚሁ የስልጠና መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም