በጋምቤላ ክልል በበጋ ወቅት 34 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ስራ ተጀምሯል

64
ኢዜአ ህዳር 12 / 2019 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል በዘንደሮው የበጋ ወራት 34 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ ። በበጋ ግብርና ልማት ስራው 70 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ቢሮው ገልጿል። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ለኢዜአ እንደገለጹት መሬቱን ለማልማት የታቀደው እርጥበታማ አፈርን ፣አነስተኛ መስኖን፣ የውሃ ፓምፖችንና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ነው። በግብርና ልማቱ ስራው አርሶና ከፈል አርብቶ አደሮችና ስራ አጥ ወጣቶች በስፋት ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ለማድረግ ባለሙያዎች ተሰማርተው የተጠናከረ የንቅናቄ ስራ በማከናወን ላይ ናቸው ብለዋል ። በአሁኑ ወቅት በተለይም የእርጥበታማ አፈርን በመጠቀም የሚከናወነው የግብርና ልማት ስራ በሁሉም ወረዳዎች የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚሁ የበጋ ወራት ስራ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል  የሰብልና የጓሮ አትክልት ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል። በዘንድሮው የበጋ ወራት ለማልማት የታቀደው መሬት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በስምንት ሺህ ሄክታር መሬት የሚሰበሰበው የምርት መጠን ደግሞ በ450 ሺህ ኩንታል ብልጫ ይኖረዋል ። እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ በተለይም የጓሮ አትክልት ምርጥ ዘር፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችና ሌሎች የምርት ግብዓቶች እየተሰራጩ እንደሚገኙ የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል ። በክልሉ የጋምቤላ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የግብርና ኤክስቴንሽ ባለሙያ አቶ ለማ ዓለማየሁ በበኩላቸው  በአሁኑ ወቅት እርጥበታማ አፈር ወይም የውሃ ሸሽ የግብርና ልማት ስራ በወረዳቸው ሙሉ ለሙሉ መጀመሩን ገልጸዋል። በወረዳው የውሃ ሸሽን በመጠቀም ለማልማት ከታቀደው 1 ሺህ 69 ሄክር መሬት መካካል አብዛኛው ማሳ ተዘጋጀቶ በበቆሎ፣ በማሽላ ፣በተማቲም፣ በሽንኩርትና ሌሎች የጓሮ አትክልት ዘሮች በመሸፈን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተለይም በአካባቢው እየጣለ ያለው ወቅቱን ያለጠበቀ ዝናብ ለእርጥበታማ አፈርን/ የውሃ ሸሽ / የግብርና ልማት ምቹ አጋጣሚ መፈጠሩንም ጠቁመዋል። በጋምቤላ ወረዳ የቦንጋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምናሴ ከሊለ በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ወቅት የእርጥበታማ አፈር እርሻ ስራ የማሳ ዝግጀት አጠናቀው በዘር የመሸፈን ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል። በግብርና ቢሮው በኩልም የጓሮ አትልት ዘሮች ፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችና ሌሎች የምርት ግብዓት  ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም