በመልካም ስነ ምግባር የተነጸ ትውልድ ለማፍራት የመገናኛ ብዙሀን በትኩረት መስራት አለባቸው---ባለስልጣኑ

46
ኢዜአ ህዳር12/2012 በመልካም ስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የመገናኝ ብዘሀንና ባለሙያዎች በህጻናት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አሳሰበ። ህጻናትን በሚመለከቱ ጉዳዮች አዘጋገብና ፕሮግራም ዝግጅት ዙሪያ  ለመገናኛ ብዙሃን  ተቋማት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወስን አንዷለም "በአዕምሮ የበለፀገና የተሻለ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት በህፃናት ላይ በትኩረት መስራት አለብን "ብለዋል። ህፃናትን ከአስተዳደግ ጀምሮ ማነፅና በስነምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ  ከወዲሁ መሆን እንደሚገባ አመልክተው መገናኛ ብዙሀን  ይህንን ጉዳይ በመዘገብ እና ተገቢው ሽፋን በመስጠት  ረገድ ዳተኝነት እንደሚታይባቸው ተናግረዋል። "ህፃናት  የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው ዛሬ ላይ መስራት ካልቻልን ጥሩ አስተማሪ፣ መሀንዲስ፣ ፓይለት፣ ዶክተርና የሀገር መሪ ማግኘት አንችልም "ብለዋል። የህፃናትን አዕምሮ ከጅምሩ ለማልማት መገናኛ ብዙሀን በዜና አዘጋገብና በፕሮግራም ዝግጅት ላይ ግልፅ ግንዛቤ ይዘው የተሻለ እንዲሰሩ ለማገዝ  መድረክ መሰናዳቱን አስረድተዋል። አቶ ወንድወስን እንዳሉት መገናኛ ብዙሀንና ባለሙያዎች  በህፃናት ጉዳይ ምን ያህል ትኩረት መስጠታቸውን በመድረኩ ይመላከታል፤ በህፃናት ዘገባና ፕሮግራም ዝግጅት ላይ የተሻለ ልምድ ያላቸው ተሞክሮዎችም ይቀርባል። በሀገሪቱ ያሉ የመገናኛ ብዙሀን  አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎች ለማሻሻል አጋዠ ግብአቶች በማቅረብ  በህጻናት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተመልክቷል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ከግልና ከመንግስት የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም