ሕዝቦች በመካከላቸው ያሉትን ችግር ፈጣሪዎች በማጋለጥ ለአገራዊ አንድነት ሊሰሩ ይገባል - የአገር ሽማግሌዎች

72
ኢዜአ ህዳር 12/2012   ሕዝቦች በመካከላቸው ያሉትን አሻጥረኞችና ልዩ ተልዕኮ ያላቸውን አካላት ለይተው በማውጣት አንድነታቸውን ማስጠበቅ እንዳለባቸው የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ። ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የኃይማኖት አባቶችናሀገር ሽማግሌዎች በክልሎቹ ባለው ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ ተወያይተው በጋራ እራት ተመግበዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር ሽማግሌዎቹ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ውጥረቱን የማርገብ ስራ እንዲሰሩ መልዕክት መላካቸውን ገልጸዋል። የሁለቱ ሕዝቦች ሁለንተናዊ መስተጋብርና አንድነት ከምንም በላይ የጠነከረ ሆኖ ሳለ የተለያዩ አካላት ልዩነቱን የሚያሰፉ ጉዳዮች እየበዙ መምጣታቸውን ተናግረዋል። በዚህ ወቅት በተለይ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ እየተስተዋለ ያለው ችግር አሳሳቢ በመሆኑ ሽማግሌዎቹ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያበረክቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አስተላልፈዋል ነው ያሉት። አቶ ንጉሱ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሕብረተሰብ ወኪሎች ግጭቶች የትኛውንም ሕዝብ እንደማይወክሉ ተረድተው የመፍትሄ አካል እንዲሆኑም ጠይቀዋል። ''መፍትሄውን እስከታች ለማድረስና መሬት እንዲደርስ ለማድረግ በየአካባቢው የእርቅና የምክክር መድረኮች ይካሄዳሉ'' ብለዋል። የአገር ሽማግሌዎቹ በበኩላቸው በመሰረታዊነት በዚህ ወቅት ''በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው ቅራኔ የህዝቡ ሳይሆን በሌሎች አካላት የተቀነባበረ ነው'' ብለዋል። ከአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ መጥተው በመድረኩ የታደሙት አቶ ምህረቴ ወንድም ውይይቱ ጠቃሚ መሆኑንና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል። ''ሁለቱ ህዝቦች ሁሉም እንደሚያውቀው በደም የተዛመዱ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ዙሪያም ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ናቸው'' ሲሉ ትስስሩን ያስረዳሉ። አሁን የተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ የሁለቱ ሕዝቦች ሳይሆን ኢትዮጵያን ማፈራረስ የሚፈልጉ አካላት የሚፈጽሙት ድርጊት እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ምህረቴ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱም በተለይ ለወጣቱ በአገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታና እውነታውን እንደሚስረዱ ገልጸዋል። ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ሮቢ ወረዳ የመጡት ታዳሚ አቶ ቶሎሳ ኪሼም የአቶ ምህረቴን ሃሳብ ይጋራሉ። አገሪቷ ወደ መጥፎ ሁኔታ እንድትገባ ያደረገው ውስጥ ውስጡን መጥፎ ስራ የሚሰሩ አካላት በመበራከታቸው መሆኑን ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙ የሕብረተሰብ ተወካዮችም ከወጣቱ ጋር በቅርበት በመሆን እስከ ታች ድረስ ወደ ሁሉም መድረስ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ገላን ከተማ የታደሙት አቶ ተስፋዬ ቱሉም እንዲሁ በየአካባቢው በአገር ሽማግሌዎች ጥሩ ስራ እየተሰራ ቢሆንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ሁሉም በየአካባቢው ሕዝቦች አንድ መሆናቸውን በመረዳት ለዘላቂ ሰላም ሲል አቅሙ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ''መሰረታዊው ችግሩ መንግስት የህግ የበላይነት በማስከበር ረገድ እያሳየ ያለው ቸልተኝነት ነው'' የሚሉት ደግሞ ከደቡብ ጎንደር ዞን የመጡት መላከ ብስራት መሓሪ ላቀው ናቸው። ''ከዚህ በፊት ሲደረግ የነበረው የፖለቲካ ሴራ አሁንም ተጠናክሮ በመቀጠሉ በተለይም በሁለቱ ህዝቦች ዘንድ ችግሩ የጸና እንዲሆን አድርጎታል'' ባይ ናቸው። ለዚህ ደግሞ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው መንግስት አካሄዱን በማስተካከል ህጋዊ እርምጃ መውስድ ሲችል እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል። የሁለቱን ክልል ህዝቦች ነዋሪዎች ካላቸው ሁለንተናዊ መስተጋብር አንጻር የማቀራረቡ ስራ ከአንድ ዓመት በላይ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል። በተለይ ደግሞ 'ኦሮማራ' የሚል ስያሜ በተሰጠው የህዝቦቹን ግንኙነት ማጠናከር መንገድ ከባህር ዳር እስከ አምቦ፣ ከደብረ ብርሃን እስከ ጂማ ማቀራረቢያ መድረኮች ተካሂደዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም