''መንገድ ለሰው ልጅ ነፃ ማድረግ '' በሚል መሪ ቃል የፊታችን እሁድ የእግር ጉዞ ይካሔዳል ።

97
ኢዜአ  ህዳር 12 / 2019  የመንገድን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ''መንገድ ለሰው ልጅ ነፃ ማድረግ '' በሚል መሪ ቃል ህዳር 14 ቀን 2019 ዓም በመቀሌ ከተማ የእግር ጉዞ እንደሚካሔድ የትግራይ ክልል ኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። ቀኑ በእግር ጉዞ የሚከበረው በተሽከርካሪዎች ፣በእግረኞችና በብስክሌተኞች ዘንድ ፍትሃዊ የመንገድ አጠቃቀም ለማረጋገጥ ታስቦ ነው ተብሏል ። በትግራይ ክልል ኮንስትራክሽን ፣ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሃለፊ ወይዘሪት ራሂል ሃይሉ   እንደገለፁት በክልሉ ከተሞች እግረኞችንና ብስክሌተኞችን በማበረታታት ከተሽከርካሪ ነጻ የሆነ ቀን ለማሰብ መሆኑን ገልጸዋል። ምክትል ቢሮ ሀላፊዋ እንደገለጹት በዋና ዋና ከተሞች ላይ የትራፊክ ፍሰትና አደጋ እየበዛ መጥተዋል ። በተለይም የግል ተሽከርካሪዎች የሚጭኑት የሰው ብዛት አነስተኛ ቢሆንም የከተሞች መንገድ በማጨናነቅ ግን ቀዳሚ ናቸው ብለዋል ። ተሽከርካሪዎቹ ለትራፊክ አደጋ መበራከት ፣  መጨናነቁን በማባባስ ፣ለድምጽና ለአየር ብክለት ምክንያት በመሆን በሰው ልጅ ጤና ላይ ተፅእኖ ማሳደራቸውን ገልፀዋል ። ችግሩን ለማቃለል ህብረተሰቡ በእግሩና በብስክሌት መጓዝ እንዲያዘወትር አልያም የህዝብ ትራንስፖርት እንዲጠቀም ለማበረታታትና ግንዘቤ  ለመፍጠር ታስቦ የፊታችን እሁድ በመቀሌ ከተማ የሶስት ኪሎ ሜትር  የእግር ጉዞ መዘጋጀቱን አስረድተዋል ። መነሻው መቀሌ አክሱም ሆቴል በሚያደርገው ይኽው የእግር ጉዞው ከሁለት ሺህ በላይ የከተማው ነዋሪዎች  ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ። እለቱን በእግር ጉዞ እንዲታሰብ የክልሉ ኮንስትራክሽን ፣ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው ተብሏል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም