የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚጥሩ ሃይሎች ጠብና ጥላቻ ውስጥ አይገቡም

79
ኢዜአ ህዳር 11/2012 የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚጥሩ ሃይሎች ምክንያት የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች ጠብና ጥላቻ ውስጥ እንደማይገቡ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ-ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ። የአማራና ኦሮሚያ ክልሎችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሰላም የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በሰላም ውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የሃይማኖት አባቶች፣ አባ-ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች ለረጅም ዘመናት ተከባበረው፣ ተዋደውና ተደጋግፈው የኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል። ይሁንና በአንዳንድ የፖለቲካ ትርፍ ፈላጊዎችና በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሳቢያ በመካከላቸው "ቁርሾ እንዳለ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ከወሬ የዘለለ አይደለም" ብለዋል። በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች መነሻን በማወቅ ችግሩን ከምንጩ መፍታት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። ቤተክርስቲያንና መስጊድ ማቃጠል ከየትኛውም የሃይማኖት አስተምህሮ ውጪ መሆኑን ያነሱት ተሳታፊዎቹ፤  እንዲህ አይነት እኩይ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የትኛውንም ብሄርና ሃይማኖት የማይወክሉ በመሆናቸው ሊወገዙ እንደሚገባም አሳስበዋል። በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር የማድረግ ሃላፊነትም የእነርሱ ቢሆንም ተሳታፊዎቹ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸውን ተናግረዋል። በውይይቱ የተሳተፉት ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፣ ወዳጄነህ ማህረነ እንዲሁም ዑዝታዝ አህመዲን ጀበል በበኩላቸው የሁሉም መብት እኩል የተከበረባት፤ የሃይማኖትና የብሄር እኩልነት የተረጋገጠባት እንዲሁም ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚከበርባት ኢትዮጵያ ማየት የሁሉም ዜጋ ፍላጎት መሆኑን አንስተዋል። ይሁንና አብዛኛው ሰው ይህ ፍላጎት ቢኖረውም በተግባር ግን ለሰላም የሚተጋ ባለመሆኑ አሁን የሚፈጠረው ግጭት እንዲባባስ ማድረጉን አልሸሸጉም። በሌላ በኩል ለዘመናት በጋራ በኖሩ ህዝቦች መካከል ችግር እንዲፈጠር በማድረግ የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም የሚያደርጉ የውጭ ሃይሎች መኖራቸውንም ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል። በልዩነት አጥር ውስጥ ቆመው ''የኛና የእነርሱ'' በሚል የሚሰላ ስሌት ለማንም የማይበጅ መሆኑን በመጠቆም። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ባለመው በዚህ የውይይት መድረክ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች  የታደሙ ሲሆን በቀጣይም  የህዝብ ለህዝብ ውይይቱ እስከ ወረዳ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም