በምስራቅ ወለጋ ከ14 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት ይጠበቃል

79

ነቀምቴ ኢዜአ ህዳር 11/2012 በ2011/2012 የምርት ዘመን ከለማው የእርሻ መሬት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት እንደሚጠበቅ የምሥራቅ ወለጋ ዞን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የሚጠበቀው ምርት በዞኑ በወቅቱ ከለማው 412 ሺህ 668 ሄክታር መሬት ላይ ነው።

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ብሩክ ጫላ ለኢዜአ እንደተናገሩት የሚጠበቀው ምርት  ሰሞኑን በመስክ በተደረገው የቅድመ ምርት ግምገማ መሰረት ተለይቶ ነው።

ይህም ካለፈው ተመሳሳይ  የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር  በ96ሺህ 450 ኩንታል ያህል ብልጫ እንደሚኖረው አመልክተዋል።፡

በ2011/2012 የምርት ወቅት በተካሄደው እንቅስቃሴ ለአርሶ አደሩ የምርት ማሣደጊያ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ በመቅረቡ እና የኩታ ገጠም አሰራር ተግባራዊ በመደረጉ የምርት ጭማሪ ይኖራል ተብሎ መጠበቁን የገለጹት ደግሞ የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽፈህት ቤት ኃላፊ አቶ እምሩ ነጋሣ ናቸው።

በሲቡ ስሬ ወረዳ የለሊሣ ቀበሌ   አርሶ አደር ይማም ሽፋ በሰጡት አስተያየት በምርት ዘመኑ በኩታ ገጠም እርሻ በመሳተፋቸው ከሌላ ጊዜ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በሄክታር 40 ኩንታል ያገኙ የነበረው የበቆሎ ሰብል አሁን እስከ 20 ኩንታል ጭማሪ እንደሚጠብቁ ጠቅሰዋል።

በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ካለሙት  አንድ ሄክታር መሬት እስከ 80 ኩንታል በቆሎ ምርት አገኛለው ብለው እንደሚጠብቁ የተናገሩት ደግሞ በጉቶ ጊዳ ወረዳ የሜጢ ቀበሌ  አርሶ አደር ሀብታሙ ዴሬሣ ናቸው።

በዲጋ ወረዳ የለሊሣ ዲምቱ ቀበሌ  አርሶ አደር ግርማ ኢታና  በተለይም የማሽላ፣የለውዝ፣የሰሊጥ እና በበቆሎ ምርት ላይ የምርት ጭማር እንደሚኖራቸው  በተስፋ እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

በዞኑ የደረሰ ሰብል ወቅቱን ከልጠበቀ ዝናብ ለመከላከልም የማሰባሰቡ ስራ  እየተካሄደ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም