የጋዜጠኞች ሙያን ለማሻሻል የሚረዳ ስልጠና ተጀመረ

139

አዲስ አበባ ኅዳር 11 ቀን 2012 በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና በቻይና መንግስት ትብብር የጋዜጠኝነት ሙያን ለማሻሻል የሚረዳ የአንድ ወር ስልጠና ተጀመረ።

ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ 100 ጋዜጠኛች መገናኛ ብዙሃንን የሚስተዋልባቸውን የክህሎት ክፍተት እንደሚሞላ የታመነበትና ለአንድ ወር የሚቆይ ስልጠና መካፈል ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው፤ ከዚህ ውስጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ተጠቃሽ ነው።

መንግስት የመገናኛ ብዙሃንን ለማሳደግና በነጻነት እንዲሰሩ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንና ስልጠናውን ከቻይና መገናኛ ብዙሃን ከመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቻይና በሚዲያው ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሻሻለችና እያደገች የመምጣቷን ተሞክሮ ለመቅሰም መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በሙያው ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ሙያተኞች ከመንግስትና ከግል እንዲሁም ከማህበረሰብ ራዲዮ የተውጣጡ ጋዜጠኞች በተመረጡና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስልጠና መዘጋጀቱንና ይህም በአገሪቱ እያታየ ያለውን የጋዜጠኝነት የስነ-ምግባር ክፍተት ለመሙላትና በተቃራኒ ጎራ ያሉትን ሚዲያዎች ለማቀራረብ ያግዛል ብለዋል።

የሚዲያ ቢዝነስ ማኔጅመንት፣ የፕሮዳክሽን ስራና የሚዲያ ፍልስፍና ምን መምሰል አለበት፣ የመገናኛ ብዙሃን እንዴት መደራጀት አለባቸው፣ ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ እንዴት መፍጠር ይቻላልና አገርና ሕዝብን በተገቢው መንገድ ማገልገል ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ስልጠናው ይሰጣል ብለዋል ዶክተር ጌታቸው።

ከአሰልጣኞቹ መካከል ቻይናዊቷ የሚዲያ ባለሙያ ሊዩ ዩ የኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ መስኮች መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው በሚዲያው ኢንዱስትሪም በጋራ ለማስራት መግባባታቸው ግንኙነቱን ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል።

ቻይና የሚዲያ ባለሙያዎችን ጨምሮ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ለኢትዮጵያዊያን የትምህርት ዕድል በመስጠት እያሰለጠነች መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን የሚዲያ ዘርፍ ለማሳደግና ጋዜጠኛው በነጻነት እንዲሰራ እያደረገ ያለው ተግባር የሚያበረታታና ሊቀጥል የሚገባው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ስልጠናው ከህዳር 11 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም