በአዲስ አበባ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በትራፊክ የ132 ሰዎች ህይወት አልፏል

81
ኢዜአ ህዳር 11/2012 አዲስ አበባ ውስጥ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት በተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ የ132 ሰዎች ህይወት ማለፉን የከተማው የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። በከተማው የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ መቀነስ ብሎም መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ የመከረ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል። የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትና ማህበራት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በተሳተፉበት በዚሁ ውይይት ላይ እንደተገለፀው በአገሪቱ የሚታየው የትራፊክ አደጋ አሁንም እየተባባሰ መጥቷል። በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአዲስ አበባ ብቻ የተከሰቱት የትራፊክ አደጋዎች እንኳ ለ132 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆነዋል፤ ከ500 የሚልቁ ሰዎችን ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት ዳርገዋል። አብዛኛው አደጋ የተከሰተው ከማሽከርከር ብቃትና ስነ-ምግባር እንዲሁም ከመንገደኞች ጥንቃቄ ጉድለት ጋር በተያያዘ መሆኑም ተመልክቷል። በመሆኑም የትራፊክ አደጋ የሚያደርሰውን ሰብአዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳት ለመከላከል በተለይ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት በስነ-ምግባር የታነጹ ብቁ አሽከርካሪዎችን የማፍራት ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና የሚሰጠው አቤት ሆስፒታል የህክምና ጥናት ዳይሬክተር ዶክተር ዮናስ ተፈሪ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል። በዚሁ ፅሁፋቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ባደጉት አገራት የትራፊክ አደጋ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አገራት ግን በአስደንጋጭ ሁኔታ አደጋው  እየጨመረ መጥቷል። በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከ5 ሺህ በላይ የሞት አደጋ የተመዘገበ መሆኑን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘ  መረጃን ጠቅሰው ያመለከቱት ዶክተር ዮናስ ይህም በአማካኝ በቀን ከ10 በላይ ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ እየተቀጠፈ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። በትራፊክ አደጋ በየቀኑ ወደ አቤት ሆስፒታል ከሚመጡት ተጎጂዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት እግረኞች መሆናቸውን አንስተዋል። በመሆኑም ይህን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አስከፊ አደጋ ለመከላከል ሁሉም ዜጋ በየፊናው የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል። የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ኃላፊዎችና የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በስነ-ምግባር የበለጸጉ ብቁ አሽከርካሪዎችን ማፍራት ይቻል ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል። እግረኞችም የእግረኛ መንገድን ብቻ በመጠቀምና በኃላፊነት ስሜት በጥንቃቄ በመጓዝ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ተጠይቀዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም