በኤሌክትሪክ መብራት መቆራረጥ መቸገራቸውን በሂንዴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

92

ነቀምቴ ኢዜአ ህዳር 11/2012 በኤሌክትሪክ መብራት መቆራረጥና መጥፋት ምክንያት በዕለት ተዕለት ኑሮቸው ላይ ችግር እንደሆነባቸው በምስርቅ ወለጋ ዞን ሂንዴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ደረጀ መኮንን እንዳሉት በከተማው ተደጋጋሚ የመብራት መቆራረጡና አንዳንዴም ለሁለት ሳምንታት ያህል ይጠፋል።።

በዚህም ምክንያት የተሰማሩበት የእህል ወፍጮ ስራ ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ በጨለማ ለማሳለፍ በመገደድ በዕለት ተዕለት ኑሮቸው ላይ ችግር እንደሆነባቸው ተናገረዋል።

በተለይ  ሰርተው ቤተሰብ ማስተዳደርና  የመንግሥት ግብር መክፈል እንዳልቻሉም ጠቁመዋል፡፡

በከተማው በልብስ ስፌት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ወጋሪ መኮንን በበኩላቸው ከመብራት አገልግሎት መቆራረጥና መጥፋት ጋር ተያይዞ መደበኛ ሥራቸውን ማከናወን  ኑሮቸውን በአግባቡ ለመምራት ችግር እንደሆናቸው ገልጸዋል።

መብራቱ በሁለት ሳምንታት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ የሚመጣበት ሁኔታ መኖሩን የተናገሩት ደግሞ በወንዶች የፀጉር ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ  ገለታ ኦልጅራ ናቸው፡፡

አቶ ገለታ እንደገለጹት ሥራውን የሚያከናውኑት በቤት ኪራይ በመሆኑ በመብራት ችግር መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው በኑሮቸው ላይ  ጫና ፈጥሮባቸዋል።

በማህበር ተደራጅተው ከመንግሥት በተመቻቸላቸው የብድር አገልግሎት 27 ሺህ ብር ተበድረው የእንጨትና የብረታብረት ሥራ ቢጀምሩም  በመብራት ችግር ምክንያት መስራት እንዳልቻሉ የገለጹት ደግሞ አቶ ዲሪባ ሠቀታ ናቸው።

በኤሌክትሪክ መቆራረጥና መጥፋት ምክንያት ሰርተው የተበደሩትን የመንግሥት ገንዘብ ለመመለስ መቸገራቸውን አመልክተዋል።

ሂንዴ ከተማ የሚገኝበት የኤባንቱ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ታደሰ ቡራዩ በበኩላቸው የኤሌክሪክ መብራት አገልግሎት ችግሩ በአካባቢያቸው የልማት  እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ሰዎችም  በችግር ምክንያት በተገቢው መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡

የዞኑ ውሃ ልማትና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጃ አበራ በበኩላቸው  ከሂንዴ በተጨማሪ የሌሎችም ወረዳዎች  ማዕከላት ተመሳሳይ ችግር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመብራት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት  የተበላሹ የኤሌክትሪክ መብራት ጠግኖ ለአገልገሎት ለማብቃት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መብራት አገልግሎት የየጊዳ አያና የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ንጉሤ አያናው ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  የደንበኞች ቅሬታ የተጋነነ ቢሆንም ችግሩ እንዳለ ገልጸዋል።

ማዕከሉ የተለያዩ ወረዳዎችን የሚሸፍን በመሆኑ  የተሸከርካሪ እጥረት ስላለበት ፈጥነው በቦታው በመድረስ ለደንበኞች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ ተናግረዋል።

ብልሽቱ የተከሰተበት ቦታ በመፈለግ ለደንበኞች ጥያቄ መልስ ለመስጠት የማዕከሉ ሠራተኞች ወደ ስፍራው  በማሰማራት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም