ከአፍራሽ ድርጊት በመራቅ ሀገራቸውን ለማገልገል እንደሚዘጋጁ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ

74

ሆስዕና ህዳር 11/2012 እራሳቸውን ከአፍራሽ ድርጊት በማራቅ ተምረው ሀገራቸውን ለማገልገል ከወዲሁ እንደሚዘጋጁ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ።

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለኢዜአ ሪፖርተር በሰጡት አስተያየት ለሀገራቸው ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እታገኝ ሴርዶሎ " ተማሪዎች ሀገራዊ ሰላማችንን ከማስጠበቅ ባለፈ በእውቀታችን ሀገራችንን የማገልገል ኃላፊነት አለብን "ብላለች፡፡

በአሁኑ ወቅት  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮች ሀገርን ከመጥቀም  ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ጠቁማለች፡፡

ተማሪዎችፍ  በማይጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የትምህርት ጊዜያቸውን  ከማባከን መቆጠብ እንዳለባቸውም አስተያየቷን ሰጥታለች።

ከአፍራሽ ድርጊት እራሳቸውን በማራቅ አብሮነታቸውና ሰላማቸውን ጠብቀው በመማር ሀገራቸውን ለማገልገል ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው የተናገረው ደግሞ  የሁለተኛ ዓመት ሲቪል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ተማሪ ናዝራዊ ሄኖክ ነው፡፡

"ያስተማረችንን ሀገር እና ህዝብ ልንክሰው  የሚገባው ሰላም በማደፍረስ እና መከፋፈልን በማስፋት ሳይሆን በእውቀት ብቁ ሆነን በማገልገል ነው" ብሏል፡፡

ሌላኛው የአራተኛው ዓመት የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ተማሪ  አበበ ተክለ ማርያም በበኩሉ አባቶች ጠብቀው ያቆየዋትን ሀገር  በአብሮነት በማስቀጠል ነገን ያለመ ሰላማዊ ሂደትን ለማኖር የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡

በጥፋት ከፈረሱ ሀገራት ትምህርት በመውሰድ  በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች  ሀገራቸውን ለመጠበቅና ለማልማት ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡

በዩኒቨርሲቲው  የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ሲሳይ ዮሀንስ በተቋሙ ተጠብቆ የቆየውን ሰላም ለማስቀጠል ትኩረት መሰጠቱን ተናግሯል።

በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን  መሰረት በማድረግ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል በተለያዩ መድረኮች ግንዛቤ የማስጨበጥ  ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን አመልክቷል።

እንደ ተማሪ ሲሳይ  ገለጻ አብሮነትን በማጠናከር የኢትዮጵያውያን መገለጫ  የሆነውን የመረዳዳት ባህል በማዳበር ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ በማሳካት  ሀገራቸውን በተገቢ እንዲያገለግሉ ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም