አልማ ከደረጃ በታች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማሻሻል አቅዷል

73

ደሴ ኢዜአ ህዳር 11 ቀን 2012 የአማራ ልማት ማህበር /አልማ / በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ አባላቱ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ በማሰባሰብ ከደረጃ በታች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል ማቀዱን በማህበሩ የደሴ ማስተባበሪያ አስታወቀ ።

ማስተባበሪያው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በያዘው እቅድና በሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር  በኮምቦልቻ ከተማ ምክክር አድርጓል ።

በማህበሩ የደሴ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው ታደሰ እንደገለጹት በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች መካከል ደረጃቸውን አሟልተው የሚያስተምሩት 17 በመቶ ብቻ ናቸው።

በተለይም በመቅደላ፣ ሳይንትና አርጎባ ወረዳዎች የሚገኙት ትምህርት ቤቶች የዳስና የሳር ክዳን ያላቸው በመሆኑ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በማሳያነት አቅርበዋል።

ተማሪዎች እንደየወቅቱ ሁኔታ ነፋስ፣ ጸሃይ፣ ዝናብና ውርጭ እየተፈራረቀባቸው ለመማር እንደተገደዱም አቶ አበባው ተናግረዋል ።

ማህበሩ በቀጣይ ሦስት ዓመት ከአባላቱ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ከደረጃ በታች የሆኑት ትምህርት ቤቶችን እንደገና በማስገንባትና በማስፋፋት ገጽታቸውን ለመቀየር እንደሚሰራ አስረድተዋል ።

እቅዱን በመተግበር ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ከ17 በመቶ ወደ 55 በመቶ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ኃላፊው ገልፀው ለስኬቱ የአመራሩና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የሚውለውን ገንዘብ ለማሰባሰብም አሁን ያሉትን የአባላቱ ቁጥር ከ900 ሺህ ወደ አንድ ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመት አምስት ደረጃቸውን የጠበቁ አዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና አንድ ሞዴል የቅደመ መደበኛ ትምህርት ቤት ይገነባሉ ብለዋል ።

በ228 የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የማስፋፊያ ግንባታ፣ እድሳት፣ በቁሳቁስና በቤተ ሙከራዎችን የማሟላት ስራ በማከናወን ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ይደረጋል፡፡

ማህበሩ የያዘውን አቅድ ለማሳካትም ከአባላትና ማህበረሰቡ በተጨማሪ ከፋብሪካዎችን፣ ባለሃብቶችና በውጭ አገር ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ጋር መስራት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል አበጋዝ በበኩላቸው በዞኑ ካሉት 1 ሺህ 298 የመጀመሪያ ደረጃ፣ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 234 የሚሆኑት ከደረጃ በታች ናቸው።

ባለፈው ዓመት የተወሰኑትን የዳስና የሳር ትምህርት ቤቶች አሻሽለናል ያሉትኃላፊው ዘንድሮም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የደረጃ ማሻሻያው በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከ70 ወደ 40 ዝቅ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል ።

የመቅደላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ማሞ በበኩላቸው ከደረጃ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶችን ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ከአልማ ጎን በመሆን የበኩላችንን ድርሻ እናበረክታለን ብለዋል ።

ወረዳው ህብረተሰቡን በማስተባበር አንድ ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የስምንት ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም