ቢሮው በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የሃይማኖት መሪዎችና አባገዳዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ጠየቀ

94

አዳማ ኅዳር 11 ቀን 2012 በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ የሃይማኖት መሪዎችና አባገዳዎች ሚናቸውን እንዲወጡ የኦሮሚያ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ጠየቀ።

የሃይማኖቶችና የብሔር ብዙኃነት አያያዝና አስተዳደር! በሚል መሪ ቃል የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረስ ዛሬ ተካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን የሃይማኖት መሪዎች እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ ሊያጎለብቱ ይገባል።

''ሁሉም ቤተ እምነቶችና መሪዎቻቸው የሰላም መዘምራን ናቸው'' ያሉት ኮሎኔል አበበ፣ ከተማውም ሆነ ክልሉ ወደ ነበረበት አስተማማኝ ሰላም እንዲመለስ ጥረቱ መጠናከር  አለበት ብለዋል።

አባገዳዎችና የሃይማኖት መሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ በማድረግ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በክልሉ የሚኖሩ ብሔሮች/ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ መክሸፉን የገለጹት አቶ አበበ፣ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንዲሰራ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ፀሐፊ አቶ ህሉፍ ወልደ ሥላሴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ  እስልምናና ክርስትና ዘመን ተሻጋሪ የአብሮነትና መከባበር እሴት መገንባታቸውን  አስታውሰዋል።

በመሆኑም ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ የፖለቲካ አሻጥር ቦታ ሊሰጠው አይገባውም ብለዋል።

መላከ ምህረት ቆሞስ አባ አሰፋ የሃይማኖት ተቋማት አስተዋይና አርቆ አሳቢ ተተኪ ትውልድ በመገንባት በየደረጃው ያሉት የሃይማኖት መሪዎች ምዕመናን በማስተማርና በመምከር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በኮንፈረንሱ ከከተማው 18ቱ ቀበሌዎች የተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎች፣አባገዳዎችና የሃይማኖት መሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም