በአዳማ ከተማ ተከስቶ የነበረው ግጭት ባስከተለው ጉዳት የተጠረጠሩ 179 ግለሰቦች ለህግ ቀረቡ

70

ኢዜአ፤ህዳር 11/2012 በአዳማ ከተማ ሰሞኑን በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የተጠረጠሩ 179 ግለሰቦች ለህግ መቅረባቸውን የከተማዋ አስተዳደርና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሁባድ ጂና ለኢዜአ ዛሬ እንደገለጹት ለህግ የቀረቡት ተጠርጣሪ ግለሰቦች ሰላማዊውን የወጣቶችን ተቃውሞ በመጠምዘዝ ወደ ግጭት እንዲያመራ ምክንያት የሆኑ ናቸው ብለዋል።

ጉዳዩን በማስተባበር፣በመምራትና በመሳተፍ ለሰው ህይወት መጥፋትና በንብረት ማውደም የተጠረጠሩ 179 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ተናግረዋል።

አዳማ ከተማ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች ተቻችለው በፍቅር አብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት ያሉት ሃላፊው ተጠርጣሪዎቹ ድንገት የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት እንደተጠቀሙበት አስረድተዋል ።

ሰላማዊ የወጣቶች ተቃውሞ ወደ ግጭት እንዲያመራና የብሔርና የሃይማኖት መልክ እንዲይዝ ያደረጉት አካላት ቀድሞውኑ ተልዕኮ የተሰጣቸውና ውስጥ ውስጡን የሁከትና ብጥብጥ ሴራ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

በከተማዋ በርካታ የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸውና የተሰወሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የፀጥታ አካላት ክትትል ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት አቶ ሁባድ ህብረተሰቡ ጥፋተኞችን በማጋለጥና አሳልፎ ለህግ በማቅረብ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ድርጊቱ የከተማዋን መልካም ገፅታና የሰላም ተምሳሌትነቷን ለማጠልሸት ብሎም በዚህ የጥፋት  ድግስ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተደረገ ጥረት መሆኑንም አመልክተዋል።

ከተማዋ ወደ ነበረችበት ሰላማዊ ሁኔታ እንድትመለስ አባገዳዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ላበረከቱት አስተዋፅኦ አቶ ሁባድ አመስግነዋል።

የቦኩ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ  መላከ ምህረት ቆሞስ አባ አሰፋ በሰጡት አስተያየት  የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን በከተማዋ ሰላም እንዲሰፍን ከመንግስት ጋር በትብብር ሲሠራ እንደነበር አውስተዋል ።

በከተማዋ በተፈጠረው የሁለት ቀናት ግጭት ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ትንሹም ትልቁም አውቆዋል ያሉት የሃይማኖት አባቱ የጥፋት ድግስ ማንንም እንደማይመርጥ መገንዝብና የከተማዋን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባ አስገዝበዋል።

በጥፋቱ የተሳተፉ ወጣቶች በፈፀሙት ድርጊት እንዲፀፀቱ ፣መንግስትንና ህዝብን ይቅርታ እንዲጠይቁ ቤተ ክርስቲያኗ የማስተማር ሥራ እያከናወነች እንደምትገኝ ገልፀዋል ።

አዳማ ከተማ በሌሎች የክልሉም  ሆነ የሀገሪቷ ከተሞች ዘንድ በሰላም ተምሳሌትነት የምትታወቅ ከተማ መሆኗን የገለጹት ደግሞ በከተማዋ የእሬቻ ቀበሌ ነዋሪ አባ ገዳ ንጉሴ ዳቢ ናቸው።

የከተማዋን ሰላምና መረጋጋት የማይፍልጉ ሃይሎች ግጭትና ሁከት በመቀስቀስ ህብረተሰቡ እንዲሸበርና በድንጋጤ ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የከተማዋ አባ ገዳዎች ከሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ከመንግሰት ጋር በመሆን የተፈጠረውን ችግር የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ሥር እንዲውል ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

አጥፊዎችንና የጉዳዩ ተዋናዮችን ህብረተሰቡ አጋልጦ እንዲሰጥና ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ በኩል አሁንም ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ።

በህገ ወጥ ድርጊት የተሳተፈ ሃይል ከተጠያቂነት እንደማይድን የገለፁት አባ ገዳው ወጣቱ እራሱን ከጥፋት ሃይሎች መሳሪያነት በመጠበቅ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም ምክራቸውን ለግሰዋል ።

በቀጣይነትም በከተማዋም ሆነ በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም