የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ውህደቱ ለአገራዊ አንድነትና ለሰላም መስፈን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገለፁ

54

ደሴ ኢዜአ ህዳር 11 ቀን 2012 የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ወደ አንድ ውሁድ ፓርቲ መሸጋገር የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥና ሰላምን ለማስፈን ገንቢ ሚና ይጫወታል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ ።

በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሰብስብ አዲስ እንደገለጹት ውህደቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል።

ይህም የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የኢህአዴግ  ውህደት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡

በፖለቲካ ተገልለው የቆዩ አጋር ድርጅቶች ኢትያጵያዊ ስሜታቸው እንዲጎለብትና በአዲስ መንፈስ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ውህደቱ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በፓርቲዎች መካከል አሁን እየተስተዋለ ያለውን የመተቻቸት፣ ያለመደማመጥ፣ ያለመናበብና የመገንጠል አባዜንም ይቀርፈዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ ከውህደቱ ጋር ተያይዞ በሚሻሻሉ መመሪያዎችና ደንቦች ላይ ምሁራን፣ ህብረተሰቡና የፓርቲው አባላት እንዲመክሩበት ቢደረግ ያለፉት ስህተቶች ዳግም እንዳይደገሙ ያግዛል።

ሌላዉ የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ሀይሉ በበኩላቸው ውህደቱ አግላይነትን ከመቅረፉ ባለፈ የኢትዮጵያን አንድነት፤ ሰላምና የመቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡

ውህደቱ ሁሉም የአገራችን ህዝብ በአገሩ ላይ በእኩልነት እንዲሳተፍና እንዲወስን በማስቻል የእኔነት ስሜትን ለማዳበር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በህዝብ ተጋድሎ የመጣውን ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢህአዴግ የነበረውን አደረጃጀት በመለወጥ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ውህደት ማከናወኑ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን አብራርተዋል ።

ይህም በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ፍትሃዊ አሰራርንና ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን ፓርቲው በቁርጠኝነት እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርለት አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው ፖለቲካ አግላይ፣ የበላይና የበታች የነበረበት ነበር ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ውህድ ፓርቲው እነዚህን ችግሮች ቀርፎ እኩል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲኖር ያደረጋል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡን በብሄርና በሐይማኖት ከፋፍለው አገርን ለማተራመስ የሚሰሩ የፖለቲካ ጥቅመኞችን ሴራ ለማክሸፍም አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም