በጋሞ ዞን በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ 31 ሰራተኞች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው

58

አርባ ምንጭ ህዳር 11 /2012 በጋሞ ዞን በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማይገባቸው ደረጃ ላይ ተቀምጠው በተገኙ 31 ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችል መረጃ ማሰባሰቡን የዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ገለፀ ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዳበሮ ዳልጬ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዞን ደረጃና በስሩ በሚገኙ ወረዳዎች የ3ሺህ 238 ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ስራ ተከናውኗል ።

ከእነዚህ ዉስጥ 31 የመንግስት ሠራተኞች በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ለበርካታ ዓመታት የመንግስትን ገንዘብ ያለአግባብ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ተረጋግጧል ፡፡

የማጣራት ሥራዉ በተጀመረበት ወቅት ሠራተኞቹ ራሳቸውን በማጋለጥ ከሚደርስባቸው ህጋዊ ቅጣት እንዲድኑ እድል ቢሰጣቸውም ራሱን ለማጋለጥ የደፈረ አንድም ሠራተኛ አልተገኘም ብለዋል ፡፡

31ዱ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ አስፈላጊውን መረጃ ለዞኑ ዐቃቤ ህግ ለማስተላለፍ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ከህገ-ወጥ ቅጥር፣ ተገቢ ካልሆነ የደረጃ ዕድገት፣ ከዝውውርና ምደባ ጋር ተያይዞ ሊፈጸም የነበረ የ131 ግለሰቦች ህገ -ወጥ ድርጊት ማስቆም እንደተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል ።

ይህንኑ ተከትሎ አለአግባብ ሊከፈል የነበረ  36ሺህ 936 ብር የመንግስት ገንዘብ ማዳን ተችሏል ።

በየተቋማቱ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለማስቀረት የቁጥጥርና የክትትል ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ዳበሮ አያይዘው ገልፀዋል ።

የጋሞ ዞን የስነ-ምግባር መከታተያ ኦፊሰር አቶ ግርማ ከተማ በበኩላቸው ከሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ ከ2005 ዓም ጀምሮ በበርካታ ግለሰቦች  ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

በጋሞ ዞን ፐብልክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ በኩል የተደረገው ማጣራት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው ጥፋተኛ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ ይደረጋል ብለዋል ።

ከመሠረታዊ የስነ-ምግባር መርሆዎች መካከል ግልጸኝነትና ህግን ማክበር ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ቢሆኑም ህገ-ወጥ ተግባራት የተፈቀዱ እስኪመስል ድረስ  ክፍተት የሚታይባቸው ተቋማት የመልካም አስተዳደር በደል ሲፈፅሙ ቆይተዋል ያሉት ደግሞ በመንግስት ስራ የሚተዳደሩ አቶ ግዛቸው ቡንዱሬ ናቸው፡፡

ከሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ የተደረገውን የማጣራት ስራ አድንቀው ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን  በግለሰቦቹ ላይ ጠንከር ያለ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም