ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብና ከተባይ ወረርሽኝ ለማዳን የእድገት ዘመናቸውን ያልጨረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ተገቢ አይደለም - ግብርና ሚኒስቴር

87
ኢዜአ ህዳር 10/2012፡-  ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብና ከተባይ ወረርሽኝ ለማዳን ተብሎ የእድገት ዘመናቸውን ያልጨረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። አርሶ አደሮችም ወቅቱን ጠብቀው የደረሱ ሰብሎችን በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነት ና ጥራትን ማስጠበቅ እንዳለባቸው አሳስቧል ሚኒስቴሩ። የግብርና ሚኒስቴር በመኸር ሰብል አሰባሰብ ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የተባይ ወረርሽን የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በ2011/12 የምርት ዘመን 13 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማልማት 382 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ነው እንደ አገር እቅድ የተያዘው። የዝናብ ስርጭቱም እስከ ጥቅምት ድረስ በመቆየቱ የቆላ ጥራጥሬ ባለመዘራቱና ገና የሚዘሩ ሰብሎች እንዳሉ ሆኖ እስካሁን 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር  መሸፈኑን ገልጿል። በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ገርማሜ ጋሩማ እንዳሉት፤ ከጠቅላላው የሃገሪቷ ምርት 40 በመቶው እስካሁን ባለው ጊዜ ተሰብስቧል። የዝናብ ዝርጭቱ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ደግሞ ከብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ የአየር ትንበያ መረጃ አረጋግጠናል ብለዋል። በተለይም ከፍተኛ ሰብል አብቃይ በሆኑት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በምርት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ወቅቱን ያልበቀ ዝናብ እንደሚጥል ይጠበቃል ብለዋል። በመሆኑም አርሶ አደሮች የተለያዩ መሳሪያዎችን ተጠቅመው የደረሱ ሰብሎችን በአግባቡ መሰብሰብ አለባቸው  እንጂ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብና ከተባይ ወረርኝሽ ለመከላከል በሚል ሰበብ ያልደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል። ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና ጥራት ያለው ምርት ለማምረት አርሶ አደሮች ከዚህ ድርጊት መታቀብ እንዳለባቸው ተናግረዋል። በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጤናና ጥራት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ወልደሃዋርያት አሰፋ በበኩላቸው የተባይ ወረርሽኝ በምርት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል። ሚኒስቴሩ ከዓለም የምግብ ድርጅት የዳሰሳ ጥናት የሚደረስውን መረጃ መሰረት በማድረግም የአንበጣ መንጋ፣ ግሪሳ ወፍና ተምችን ለመከላከል ቀድሞ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች የተከሰተውን አንበጣ መንጋ መከላከል ተችሏል ነው ያሉት። በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልሎች ተከስቶ የነበረውን የግሪሳ ወፍንም የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል ተችሏል ብለዋል። በተጨማሪም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኮምቦልቻ አካባቢ የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። በአጠቃላይ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋና ግሪሳ ወፍ ያደረሱት ጉዳት በባለሙያዎች እየተጠና በመሆኑም ሲጠናቀቅ ውጤቱ እንደሚገለጽ ተናግረዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም