ቮይዝ ኩባንያ የግልገል-ጊቤ ሁለትን የግንባታ ውል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

72

ኢዜአ፤ህዳር 11/2012 ቮይዝ የተሰኘው የጀርመን ኩባንያ የግልገል-ጊቤ ሁለት የሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሁሉን አቀፍ የኦፕሬሽን ስራ ለማማከር የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮዽያ ጋር መፈራረሙን  ይፋ ሆኗል።

ዋተር ፓወር ማጋዚን በድረ ገፅ ዘገባው  እንዳስነበበው፤የመግባቢያ ስምምነቱ የተፈረመው በጀርመኗ በርሊን ከተማ የቡድን 20 ሃገራት የኢንቨስትመንት ስብሰባ እያካሄዱ በነበረበት ወቅት መሆኑን መረጃው ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሃይል ሚኒስትሩ ስለሽ በቀለ (ዶ/ር) እና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የቮይዝ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማርክ ክላሰን ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን፤ በመግባበቢያ ስምምነቱ ወቅትም የጀርመን ፌደራል ኢኮኖሚክ እና የሃይል ሚኒስትር ፒተር አልማየር መገኘታቸውን መረጃው አክሏል፡፡

 በሁለት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው የግንባታ አግልግሎት እና ማማከር ስራ ዋና ዓላማው 420 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ነው ተብሏል፡፡

አማካሪ ኩባንያው የአቅርቦት ስፋትን፣ የስርዓተ-ዝርጋታ ዘመናዊነትን እና የዲጂታል መፍትሄ አፈፃፀምን በሚመለከት ልዩ የስልጠና ፕሮግራም በመስጠት የዕውቀት ሽግግር እንደሚያደርግም ዘገባው አትቷል፡፡

ሁሉም በግልገል-ጊቤ የሃይል ማመንጫ የሚከናወኑ የስራ እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያዊያን የኩባንያው ባለሙያዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል፡፡

“የግልገል-ጊቤ ሁለትን የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም መጓተት በትንሹም ቢሆን ቀንሰን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር በመሆን ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንፈልጋለን” ያሉት ደግሞ በኩባንያው የምስራቅ አፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ማርክ ክላሴን ናቸው፡፡

የተረጋጋ እና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት መገንባት ለኢትዮጵያ እና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራትም ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማታቸው  መሠረት መሆኑም ተገልጿል።

ግልገል-ጊቤ ሁለት ከዋና ከተማ አዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ በኩል 300 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኑን ያሳየው ዘገባው፤ ኩባንያው ሃይል ማምረት የሚችሉ አራት ፔልተን ተርባይኖችን እና ጀኔረተሮችን እንዲሁም የመካኒካል እና ኤሌክትሪክ መሳሪያዎችን በማበርከት የሃይል ኦፕሬተር ሰራተኞችንም አሰልጥኖ አዘጋጅቷል ብሏል፡፡

የግልገል-ጊቤ ሁለት የሃይል ማመንጫ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት 15 በመቶ በሚሆኑ የኢትዮጵያ መንደሮች በሃይል የተሳሰሩ ሲሆን በአሁን ወቅትም ግማሽ የሚሆኑት የገጠር ሰፈሮች ሃይል እንደሚያገኙ ዘገባው ጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ካሉ ሃገራት መካከል ጥልቅ የውሃ ሃብት ያላት መሆኗን የጠቆመው ዘገባው 45 ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላትም ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ2011 ጀምሮ የታዳሽ ሃይል ልማት ፕሮጀክትን በመደገፍ በምስራቅ አፍሪካም የሃይል ማዕከል ለመሆን እየተጋች ያለች ሃገር ናት በማለት ዋተር ፓወር ጋዜጣ  በዘገባው አስፍሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም