የዞኑ አርሶ አደሮች ኮምባይነር ተጠቅመው በ300 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ምርት ሰበሰቡ

147
ደብረ ማርቆስ ኅዳር 11/ 2012 የምሥራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች በዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ መሣሪያ(ኮምባይነር) ተጠቅመው በ300 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ስንዴ መሰብሰባቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። አርሶ አደሮች ኮምባይነር ዘርፈ ብዙ ጥቅም  እንዳስገኘላቸው ይናገራሉ። አርሶ አደሮቹ 13 ኮምባይነሮች ተጠቅመው ስንዴውን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ  መሰብሰባቸውን የመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ እያለ ዳኛ ለኢዜአ ገልጸዋል። በዚሀም ከ600 በላይ አርሶ አደሮች ከ11ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል። የአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እየጨመረ በመምጣቱ ሰብሉን ለመሰብሰብ 80 ኮምባይነሮች ተጠይቀው እንደነበር አስታውሰዋል። ዞኑ ትርፍ አምራች ከመሆኑ አኳያ ተያይዞ በኩታ ገጠም የተዘራ ከ240ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል ለመሰብስብ  ኮምባይነሮች እንደሚያስፈልጉ ባለሙያው  አመልከተዋል ። ኮምባይነሮቹ ባልገቡባቸው አካባቢዎች  የሚገኙት አርሶ አደሮች  ያቀረቡትን የኮምባይነር  ጥያቄ ለማሟላት ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዞኑ ከ145ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በኩታ ገጠም ስንዴ መሸፈኑንም አቶ እያለ ተናግረዋል። በባሶ ሊበን ወረዳ የዶገም ቀበሌ አርሶ አደር አዘነ አትንኩት በኩታ ገጠም ያለሙትን አንድ ሄክታር ተኩል ስንዴ  በኮምባይነር ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ መሰብሰባቸውን ይገልጻሉ። ምርቱን በሰው ጉልበት ለመሰብሰብ ቢሞከር ኖሮ፤ ከ15 ቀናት በላይ ይወስድበኝ ነበር ብለዋል። ከአጨዳ እስከ ውቂያ ድረስ ያለው የምርት አሰባሰብ ሂደት በኮምባይነር መከናወኑ የምርት ብክነትን እንዳስቀረም ተናግረዋል። የጎዛምን ወረዳ የቸር ተከል ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ጌታቸው ቢሻው ባለፈው ዓመት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የነበራቸውን ስንዴ በሰው ኃይል  ለመሰብሰብ ልጆቻቸውን ከትምህርት በማስቀረትና ከአራት በላይ የጉልበት ሠራተኞች ቀጥረው ለ13 ቀናት ማሰማራታቸውን አስታውሰዋል። ሆኖም በዚህ ዓመት በኮምባይነር ተገልግለው 46ኩንታል ስንዴ 3 ሺህ 500ብር ከፍለው መሰብሰባቸውን አስታውቀዋል።የጊዜና የጉልበት ብክነት ቅነሳውን በንጽጽር በማሳያነት ጠቅሰዋል። በዞኑ በምርት ዘመኑ በሰብል ከተሸፈነው 649ሺህ ሄክታር ማሳ ከ22ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም