የአየር ንብረት ለውጥ ወደ 7ሺ የሚጠጉ የአፍሪካ የዕፅዋት ዝርያዎች ላይ የመጥፋት ስጋት አሳድሯል ተባለ

70
ህዳር 11/2012 የአካባቢያዊ የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰዎች ኑሮ መሻሻል በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ 7ሺ የዕፅዋት ዝርያዎች ለይ የመጥፋት ስጋት መጋረጡን ጥናትን ዋቢ ያደረገው የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል። ተመራማሪዎች በአፍሪካ ወስጥ ከሚገኙ ከ22ሺ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች ውስጥ 7ሺ የሚሆኑት አደጋ እንደተጋረጠባቸው መናገራቸውንም ዘገባው አክሏል። የብዝሃ ሕይወት መጥፋት ስጋት እያደገ የመጣው በሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መቀየር እና በመሬት አጠቃቀም ላይ እየታዩ ያሉ ለውጦች እንደሆነም ጥናቱ አሳይቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ ለዕፅዋት ዝርያዎች መጥፋት  ከፍተኛውን ድርሻ ሊወስድ እንደሚችልም ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ። የጥናቱ ባለሙያዎች  ጠለቅ ያለ ምልከታ ካደረጉ በኋላ በኢትዮጵያ ፣ በመሃል ታንዛኒያ፣ በደቡባዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ ዕፅዋቶች እና የምዕራብ አፍሪካ ደኖች በይበልጥ የመጥፋት ስጋት እንደተጋረጠባቸው ማረጋገጣቸውን ዘገባው አስነብቧል። ተመራማሪዎቹ በሞቃታማ የአፍሪካ አካባቢዎች በሚገኙ 22ሺ 36 የዕፅዋት ዝርያዎች ላይ ምርምር ያደረጉ ሲሆን 32 በመቶ የሚሆኑት የዕፅዋት ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸውም ጠቁመዋል። እንደ ተመራማሪዎቹ በርካታ ሀገራት ብዙ የዕፅዋት ዝርያዎች የጠፋባቸው መሆኑና  በኢትዮጵያ ግን እጅግ በጣም የተሻሉ እና ሌላ ቦታ የማይገኙ የዕፅዋት ዝርያዎች እንደሚገኙ በጥናቱ ተደርሶበታል። የሀገርቱ ደጋማ አካባቢዎች ከተጠቁ አስር አከባቢዎች አንዱ ሲሆን 50 በመቶ የሚሆኑት የሞቃታማ አከባቢ ዕፅዋቶች ጉዳት ሊደረሰባቸወ እንደሚችል በጥናቱ ተገልፅዋል። በአፍሪካ ውስጥ አንድ  ሦስተኛው የሚሆኑ በሞቃታማ አከባቢዎች የሚገኙ የዕፅዋት ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ጥናት አመላክቷል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም