በቦረና ዞን በ15 ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች የ45 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጠረ

108
ነገሌ ኢዜአ ህዳር 10/2012 ..... በቦረና ዞን በ15 ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች የ45 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩን የዞኑ ምግብ ዋስትናና የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር በበኩሉ የማህበራቱን የገበያ ትስስር ለማጠናከር ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱን ገልጿል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የገበያ ልማት ባለሙያ አቶ አጥናቸው ቶልቻ እንዳሉት ትስስሩ ማህበራት ከማህበራት ፣ ከነዋሪችና ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ ባለፉት አራት ወራት በገበያ ትስስር ተጠቃሚ የሆኑት በህብረት ስራ ማህበር የተደራጁ ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶች ናቸው ብለዋል ። የገበያ ትስስሩ የተፈጠረው በግንባታ ፣ በኢንደስትሪ ፣ በግብርና ፣ በማህበራዊ አገልግሎትና በንግድ የስራ ዘርፎች ለተደራጁ ወጣቶች መሆኑን አቶ አጥናቸው ተናግረዋል ። ማህበራቱ ትምህርት ቤቶችን ፣ መንገድና ድልድይ ለመስራት የቢሮ ውስጥ መገልገያዎችና የሰራተኞች የደንብ ልብስ ለማቅረብ ስምምነት ተፈራርመዋል ፡፡ የገበያ ትስስሩ ተጠቃሚ ከሆኑ የህብረት ስራ ማህበራት አባላት ውስጥ 1 ሺህ 155 ሴቶች ናቸው ተብሏል ። በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ የያቤሎ ጽህፈት ቤት የገበያ ትስስሩን ለማጠናከር ባለፉት አራት ወራት ብቻ 23 ሚሊዮን 412 ሺህ ብር ብድር ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ገመቹ ኮሬራ እንዳሉት ብድሩን የወሰዱት በ212 የህብረት ስራ ማህበር የተደራጁ 646 ወጣቶች ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ያቤሎ ቅርንጫፍ በዚህ አመት እስከ 80 ሚሊዮን ብር ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡ ማህበራቱ በብድር ከወሰዱት ገንዘብ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ 6 ሚሊዮን ብር ተመላሽ ማድረጋቸውንና 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መቆጠባቸውን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ተልተሌ ከተማ በጎዳናና ጂሎ ስም በእንጨትና ብረታብረት ስራ የተደራጁት አምስት ወጣቶች የገበያ ትስስሩ ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ የማህበሩ አባል ወጣት ሰለሞን ወንድሙ እንደተናገረው ባልደረቦቹ ባገኙት የ80 ሺህ ብር ብድር የቢሮ ውስጥ መገልገያ እቃዎችን በማምረት ለተጠቃሚዎች እያቀረብን ነው ብሏል፡፡ ለማምረቻ ቦታ ኪራይ ለግለሰብ በወር እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ እየከፈልን በመሆኑ የማምረቻ ቦታ ቢሰጠን የበለጠ ተጠቃሚዎች መሆን እንችላለንና የሚመለከተው አካል ያስብበት የሚል ጥቆማ አቅርቧል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም