የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች የደረሱ የአቅመ ደካማ አረጋውያንን ሰብሎች ሰበሰቡ

53
ህዳር 11/2012 "በአቅም ማጣት ምክንያት ሜዳ ላይ ቀርቶ የነበረውን የደረሰ ሰብላችን በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሰብሰቡ ወገን አለን ብለን እንድንኮራ አድርጎናል" ሲሉ በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ አቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ገለጹ።፡ የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ትናንት ባካሔዱት ዘመቻ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች የደረሰ ሰብል ሰብስበዋል ። በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የ85 ዓመቱ አዛውንት አቶ ጣፈጠ አለሙ እንደገለፁት ሁለት ጥማድ መሬታቸውን በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጤፍ ተዘርቶ ለአጨዳ ሲደርስም በወጣቶቹ እንደተሰበሰበላቸው ተናግረዋል ። ‘’በወጣቶች ድጋፍ የተዘራልኝ ሰብል ቢደርስም ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ከጥቅም ውጭ ይሆንብኛል" በሚል ስጋት ተስፋ ወደ መቁረጥ አምርቼ ነበር ብለዋል ። ሆኖም ግን የሰቆጣ ከተማ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ወደ ማሳቸው በመምጣት ሰብሉን እንዲሰበሰብ በማድረጋቸው መደሰታቸውን አስረድተዋል። ወጣቶቹ ላበረከቱላቸው በጎ ተግባር እድሜና ጤና እንዲሰጣቸው በመመኘት ሁሉጊዜም ይህንን በጎ ተግባራቸው እንዲቀጥሉበት  አደራ ብለዋል ። ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ዘርፌ ጥጋቡ በበኩላቸው በወጣቶቹ አራት ጥማድ የደረሰ የጤፍ ሰብላቸው እንደተሰበሰበላቸው ገልጸዋል። አቅመ ደካማ በመሆናቸው ምክንያት በአጎራባች ያለው ሰብል በሙሉ ሲሰበሰብ የእርሳቸው ብቻ ማሳ ላይ ቀርቶ እንደነበር አስታውሰዋል ። ሆኖም ግን በጎፈቃደኛ ወጣቶች ሰብላቸውን ወቅቱ ባልጠበቀ ዝናብ ለጉዳት ሳይዳረግ ስለሰበሰቡላቸው እፎይታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል ። ከክረምት የዘር ወቅት ጀምረው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት  በመሳተፍ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መምጣታቸውን የተናገረችው ደግሞ ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ወጣት አፀደ ሃጎስ ናት። በአሁኑ ወቅትም የአንበጣ መንጋና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተለይም ለአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ስጋት በመሆኑ ያልተሰበሰቡ ሰብሎችን ለመሰብሰብ እንዳነሳሳቸው ተናግራለች ፡፡ የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ማህበር አስተባባሪ ወጣት ኢሳያስ ሞገስ በበኩሉ በትናንትናው እለት ከ50 በላይ የማህበሩ አባላት በዘመቻ የአራት አቅመ ደካማ አርሶ አደሮች የጤፍ ሰብል እንደሰበሰቡ ተናግሯል ። የአቅመ ደካማና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያንን ሰብል የመሰብሰብ ስራው ወጣቱን በማስተባበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከአስተባባሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። በሰቆጣ ከተማ ወጣቶች እያደረጉ ያለውን የበጎ ፈቃድ ተግባር በሌሎች ወረዳዎች ለማስፋት በቅንጅት ይሰራል ያለው ደግሞ የዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ወጣቶች ማህበር አስተባባሪ ወጣት ከፍያለው ማለፉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ስጋት ሆኖ ያለውን የአንበጣ መንጋና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ወጣቶችን በማስተባበር  በሰብል ማሰባሰቡ ስራ በንቃት እንዲሳተፉ ይደረጋል ብሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም