በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱ እንደቀጠለ ነው

145
ደብረብርሃን ኢዜአ ህዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ሳይገድበው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን አጠናክሮ ማስቀጠሉን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ። በሚቀጥለው ሳምንት ለሚጀምረው የቀዳሚው መንፈቀ ዓመት አጋማሽ /ሚድ/ ፈተና ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው በማጥናት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አህመድ መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ቀናት በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ከተከሰተው ችግር ጋር ተያይዞ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲም መጠነኛ አለመረጋጋት ተፈጥሮ ነበር ። አለመረጋጋቱ የተከሰተው በማህበራዊ ሚድያዎች የሚለቀቁ የተጋነኑ መልክቶችና የሃሰት መረጃዎች ከፍተኛ ተጽእኖ በማሳደራቸው መሆኑን ገልጸዋል። ከዩኒቨርሲቲው ውጭ አንድ ተማሪ ሞቶ በመገኘቱ የማህበራዊ ሚዲያዎች ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ብጥብጥና እልቂት እንደተከሰተ አድርገው መዘገባቸው የተሳሳተ እንደነበር አውስተዋል። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሳይቋረጥ እስከ አሁን ቢቀጥልም ይህን እውነታ የማህበራዊ ሚዲያው ማሳየት አለመፈለጉን ተናግረዋል። አብዛኛው ተማሪ ትምህርቱን በመከታተል ላይ መሆኑን ጠቁመው በማህበራዊ ሚዲያ ተደናግረው ጊቢውን ለቀው የወጡ አንዳንድ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰው ትምህርታቸውን እንፈዲከታተሉ አሳስበዋል። በዩኒቨርሲቲው የመካኒካል ኢንጂነሪንግ 3ኛ ዓመት ተማሪ የአማኑኤል አዲስ በሰጠው አስተያየት  እስከ አሁን ድረስ በዩኒቨርስቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንደቀጠለ ነው ብሏል። ከጊቢ ውጭ በአንድ ተማሪ ላይ የተፈጠረው ክስተት በሁሉም ተማሪዎች ላይ መደናገጥ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም የመማር ማስተማር ስራው ግን ሳይቋረጥ መቀጠሉን ተናገራል። ከጊቢው የወጡ አንዳንድ ጓደኞቹን ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ስልክ ደውሎ በመጥራት የበኩሉን እገዛ ማድረጉን አስረድቷል ። ሌላው የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ሐብታሙ ደመወዝ በበኩሉ በዩኒቨርሲቲው በሚቀጥለው ሳምንት ለሚሰጠው የሴሚስተሩ ወሰነ አጋማሽ ”ሚድ” ፈተና ከባልጀሮቹ ጋር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል። ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱ አንዳንድ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በከንቱ ከማባከን ወደ ትምህርት ገበታቸውን ተመልሰው እንዲቀላቀሉ በስልክ እየጠራቸው መሆኑንም ተናግሯል ።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም