በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚውል ድጋፍ ተገኘ

68
ህዳር 10/2012በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ በጎ ፍቃደኞች በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚውል ድጋፍ ማመቻቸታቸውን የበጎ ፍቃደኞቹ አስተባባሪ ገለጹ። አስተባባሪው  አቶ ወንድሙ ካባው ለኢዜአ እንደገለፁት በአስተዳደሩ የተከሰተው ድርቅ የምግብ እህል እጥረት አስከትሏል። በዚህም ምክንያት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከወር በፊት ጀምሮ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ሲከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል። የብሄረሰብ አስተዳደሩ ተወላጆች እና ሌሎች በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር እስካሁን ባሰባሰቡት ከ650 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ 620 ኩንታል በቆሎ ግዥ መፈጸሙን  አመልክተዋል። የተገዛው የምግብ እህልም ዛሬ  ለዋግ ልማት ማህበር ማስረከባቸውን ያመለከቱት አስተባባሪው "በማህበሩ  ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲደርስ  ይደረጋል" ብለዋል። የዋግ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባምላኩ አበበ በበኩላቸው በበጎ ፍቃደኞች የተደረገው የምግብ እህል  ድጋፍ የኢትዮጵያውያን የነበረ የመረዳዳት ባህል ጎልቶ የታየበት መሆኑን በመግለጽ  አመስግነዋል። ልማት ማህበሩም የተደረገውን ድጋፍ ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር  መረዳት ለሚገባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲደርስ የሚደርግ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደምም ከቀይ መስቀል ማህበር 800 ኩንታል አልሚ ምግብ እና ቁሳቁሶችን በእርዳታ በማግኘቱ በዝቋላ እና ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳዎች ድጋፍ ለሚሹ ማህበረሰቦች መከፋፈሉን ጠቁመዋል። ድርቁ በሰውና በእንስስት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደስታ ናቸው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም