ማዕከላዊ ኮሚቴው የአዴፓን 39ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል

92

ኢዜአ፤ ህዳር 10/2012 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ/ 39ኛ ዓመት የምስረታ በዓልል ምክንያት በማድረግ ከየፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ  መግለጫ ሰጥቷል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው እንኳን ለዚህ ታሪካዊ ቀን አደረሳችሁ በማለት ድርጅቱ ብዙ ውጣውረዶችን አልፎ ለዛሬው በዓል በመድረሱ የተሰማውን ደስታ በመላ አባላቱና በትግሉ ደጋፊዎች ስም ገልጿል፡፡

የማዕከላዊ ኮሚቴው ሙሉ መግለጫ

የተከበራችሁ የአማራና መላ የሃገራችን ህዝቦች፣ የአዴፓ አባላትና የትግሉ ደጋፊዎች

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ/ የአማራና መላ የኢትዮጵያ ህዝቦችን መብትና ጥቅም የሚያስከብር የትግል ችቦ ከለኮሰ እነሆ 39ኛ ዓመቱን ያዘ፡፡ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንኳን ለዚህ ታሪካዊ በዓል አደረሳችሁ ይላል፡፡ ድርጅቱ ብዙ ውጣውረዶችን አልፎ ለዛሬው ታሪካዊ በዓል በመድረሱ የተሰማውን ደስታም በመላ አባላቱና በትግሉ ደጋፊዎች ስም ይገልፃል፡፡

የተከበራችሁ የአማራና መላ የሃገራችን ህዝቦች፣ የአዴፓ አባላትና የትግሉ ደጋፊዎች

ድርጅታችን በ39 ዓመታት የትግል ዘመኑ ባስመዘገባቸው ድሎች በትግሉ ሂደት ባጋጠሙት ፈተናዎችና ፈተናዎቹን ለማለፍ በየመድረኩ በከፈለው መስዋዕትነት ሲለካ አዴፓ እውነትም የፅናትና የውጤት ተምሣሌት ነው፡፡

የአዴፓ ታጋዮችና የትግሉ ደጋፊዎች የድርጅታችን የምስረታ ታሪክ ከ38 ዓመታት የትግል ጉዞ በኋላ ራሱን እየደገመ መሆኑን ከሚያረጋግጥ እውነት ፊት ቆመናል፡፡ የድርጅታችን ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚሁ በህዳር ወር ባካሄደው ስብሰባ ኢህአዴግ ከግንባርነት ወደ አንድ ወጥ ፓርቲነት እንዲሸጋገር በጥናት ላይ የተመሠረተ አቋም ወስዷል፡፡ ከሥራ አስፈፃሚያችንና ማዕከላዊ ኮሚቴያችን ውሣኔ በኋላ ውይይት ያካሄደውና በየደረጃው የሚገኘው አመራራችንና አባላችንም በውሣኔው ዙሪያ የተሟላ ሊባል የሚችል ስምምነት ፈጥሯል፡፡ ድርጅታችን አዴፓ የህዝባችንን አብሮነትና የጋራ ጥቅም የሚያረጋግጥ ህብረ ብሔራዊ አንድነት መገንባት ከምንችልበትና ከሚገባን ጊዜ ላይ ደርሰናል ብሎ ያምናል፡፡ ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር በመጣመርና በመተባበር ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አገር በመገንባት ጥንካሬዎቹን በማቀብና ድክመቶቹን በማረም የመጪው ዘመን ውጤታማ መሪ ሆኖ ለመገኘት ተዘጋጅቷል፡፡ በለውጥ መንፈስ ለረጅም ጊዜ በድርጅታችንና በህዝባችን ውስጥ ሲብላላ የቆየው የለውጥ አጀንዳም ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተቃርቧል፡፡ እናም የአማራና መላ የሃገራችን ህዝቦች፣ የድርጅታችን አባላትና የትግላችን ደጋፊዎች እንኳን ለዚህ አደረሰን፣ እንኳን ደስ አለን እንላለን፡፡

የተከበራችሁ የአማራና መላ የሃገራችን ህዝቦች፣ የአዴፓ አባላትና የትግሉ ደጋፊዎች

ድርጅታችን አዴፓ በ39 ዓመታት የትግል ዘመኑ በአመራና በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ልብ ውስጥ በወርቃማ ማህተም ታትመው የሚኖሩ እጅግ ብዙ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በድርጅታችን ውስጥ ተንሰራፍተው የቆዩት የአድርባይነትና የፀረ-ዴሞክራሲ ችግሮች እርስ በራሳቸው እየተመጋገቡ እኛን የለውጥ ታጋዮቹን ብቻ ሣይሆን ሰፊውን የአማራ ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለውታል፡፡ የዘንድሮውን 39ኛ ዓመት በዓላችን ልዩና ታሪካዊ ያደረገው ሁለተኛው ምክንያትም ድርጅታችን አዴፓ አንድ ዓመት ተኩል ባስቆጠረው አዲስ የለውጥ ማዕበል አማካኝነት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አድርባይነትና ፀረ-ዴሞክራሲን ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችለው ትክክለኛ አቅጣጫ መያዙ ነው፡፡

ትግላችን ከዘመን ዘመን ተሸጋጋሪ ነው፡፡ በድርጅታችን ውስጥ በጊዜ ሂደት እየተጠራቀሙ አገርና ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉባቸው ድክመቶች የሚታረሙትም በትግል ሂደት ነው፡፡ ያም ሆኖ ድርጅታችን አዴፓ በለውጡ አማካኝነት ባስመዘገበው አዲስ ድል ምክንያት በአንድ በኩል የአማራ ብሔርተኝነት ወደኋላ እንዳይመለስ በጥፍሩ ቆሞ ከሚሰራበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ አማራነት ከሌሎች ማንነቶች ጋር ፍፁም ተስማምቶ ለጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ከመቼውም ጊዜ የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክትበት እድል እንዲፈጠር መተኪያ የሌለው አመራር ከሚያረጋግጥበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

በመሆኑም ድርጅታችን በመጨው ጊዜ በለውጡ ሂደት ነጥረው የወጡ የአማራ ህዝብ አጀንዳዎች በሁሉም የትግሉ ባለድርሻ አካላት እምነት፣ ተሳትፎና ውሣኔ አስተማማኝ ምላሽ እንዲያገኙ በፅናት ይታገላል፡፡

የተከበራችሁ የአማራና መላ የሃገራችን ህዝቦች የአዴፓ አባላትና የትግሉ ደጋፊዎች

ድርጅታችን አዴፓ በኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ ደምቀው የሚታዩ ብዙ አሻራዎች አሉት፡፡ ድርጅታችን በኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ ካስቀመጣቸው ደማቅ አሻራዎች መካከልም ለህዝቦች የጋራ መብትና ጥቅም መከበር ያካሄደው ወጥ ተጋድሎ በቅድሚያ የሚጠቀስ ነው፡፡ አዴፓ ከምስረታው እስካሁን ድረስ በሃገራችን ብዝሃነትን በአግባቡ የሚያስተናግድ የፌዴራል ስርዓት እንዲገነባ፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንደየስተዳድሩና የህዝቦች እኩልነትና ነፃነት የሚረጋገጥበት የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር ታግሏል፡፡ ለእነዚህ ወሣኝ ህዝባዊ አጀንዳዎች በትግል ዘመኑ ሁሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ወደ ፊትም ለእነዚህና ለሌሎች ህዝባዊ አጀንዳዎች በፅናት ይታገላል፡፡

ድርጅታችን የአማራን ህዝብ በማስተባበር ለሰላም ለዴሞክራሲና ለፍትህ ባካሄደው ትግል ታሪክ የማይረሳው የአውደውጊያ ገድል ከመፈፀሙም በለይ በወቅቱ የትጥቅ ትግል አውጀው የተደራጀ ፖለቲካዊ አመራር ማግኘት ለማይችሉ ሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች የመታገያ መድረክ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ድርጅታችን ክልላችንን በመራባቸው ሁለት አስርት ዓመታትም በሁሉም መስክ የማይናቁ ድሎች አስመዝግቧል፡፡ ከድሎቹ ሁሉ የመጀመሪያው ድል የአማራ ህዝብ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት አዲስ ነባራዊ ሁኔታ መፍጠሩ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ባለፉት ዘመናት በሙሉ በሁሉም ቦታ ከሁሉም ህዝቦች ጋር ተዛምዶና ተጋምዶ ኖሯል፡፡ በማንነቱ ዙሪያ ተሰባስቦ ራሱን በራሱ ማልማት የጀመረው ግን ድርጅታችን ክልላችን በመራባቸው ዓመታት ነው፡፡ ከለውጥ በኋላ ደግሞ የአማራ ብሔርተኝነት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ በመሆኑም ከአሁን በኋላ በውህድ ፓርቲ ውስጥ ሆኖ የሚሠራው የድርጅታችን አመራር አማራነት በኢትዮጵያዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት በአማራነት እንዲደምቅ ጠንክሮ ይሰራል፡፡ ከለውጥ በኋላ ጐልብቶ የወጣው የአማራ ብሔርተኝነት ለፅንፈኝነት ሳይጋለጥ ለሃገራችን ብልፅግና እንዲውልም መጪውን ዘመን በሃሣብ ልዕልና ለመምራት ይተጋል፡፡

ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ/ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት በብዙ ችግሮች ተከብቦ ጭምር የአማራንና መላ የክልላችንን ህዝቦች ተጠቃሚ ለሚያደርግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ አበክሮ ሰርቷል፡፡

የተከበራችሁ የአዴፓ አመራሮችና አባላት መላ የትግላችን ደጋፊዎች

ድርጅታችን በአማራ ክልልም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ ያስመዘገባቸው ውጤቶች የተገኙት በአመራራችን፣ በአባላችንና የትግላችን ደጋፊዎች የአመራር ብቃት ቁርጠኝነትና ታታሪነት ነው፡፡ በሁሉም ዘርፍ በተመዘገቡ ውጤቶች ዙሪያ ለፈፀማችሁት አኩሪ ተጋድሎ ድርጅታችን አዴፓ ከልብ ያመሰግናችኋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በውስብስብ ችግሮች ወስጥ ነን፡፡ በመጪው ጊዜ በለውጥ ትግል የከፈትነውን የዴሞክራሲ ምህደር የበለጠ በማስፋት የራሳችንንና የህዝቦችንን ዴሞክራሲያዊ ህይወት ማሻሻል ይኖርብናል፡፡ አሁንም በገጠር የአርሶ አደሩን ምርታማነትና አኗኗር፣ በከተሞች የሰፊውን ህዝብና የመንግስት ሠራተኛውን ህይወት ለማሻሻል የሚያስችሉ ፕሮግራሞች በመቅረፅ ለአዲስ እመርታ ጠንካራ ትግል ማካሄድና ቁርጠኛ አመራር ማረጋገጥ አለብን፡፡ በገጠርና በከተሞች የተንሰራፋውን የሥራ አጥነት ችግር በሁለንተናዊ ልማት ለማቃለል ከመቼውም ጊዜ በላቀ ቁርጠኝነትና የኃላፊነት ስሜት መስራት ይጠበቅብናል፡፡

የምንገኝበት የትግል መድረክ የዴሞክራሲ ምህዳራችንን በማጥለቅ የለውጡን ትሩፋቶች ማስፋትና ለውጡን ተከትለው ብርቅየ መሪዎቻችንን እስከማጣት ያደረሱንን ተግዳሮች በብቃት ማረምና ማስወገድን የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም የህግ የበላይነትን ከማስከበር፣ የሥራ አጥነት ችግሮችን ትርጉም ባለው ደረጃ እስከመፍታት በህብረ-ብሔራዊ የአመራር ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ለላቀ ስኬት እንድንረባረብ ድርጅታችን ያሳስባል፡፡

የተከበርከው የአማራ ህዝብ፣ የተከበራችሁ የክልላችንና መላ የሃገራችን ህዝቦች

በ39 ዓመታት የትግል ዘመናችን የድርጅታችንን ተክለ ቁመና የቀረፃችሁት አማራ፣ የአማራ ክልልና መላ የሃገራችን ህዝቦች ናችሁ፡፡ በትግል ዘመናችን ሁሉ ከድርጅታችን ጐን ተሰልፋችሁ ባካሄዳችሁት ዘርፈ ብዙ ትግል አሁን ለደረስንበት የለውጥና የእድገት ደረጃ በቅተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአመራራችንና የአማራ ህዝብ መናበብ በፈጠረው የለውጥ ማዕከበል ሣቢያ ድርጅታችን እመርታዊ እድገት አሳይቷል፡፡ በመሆኑም አዴፓ በመጪው ጊዜ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በአማራ ህዝብ ዙሪያ የተያዙ የተዛቡ የታሪክ አቋሞችን በጥናትና በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለማረም በተሟላ ቁርጠኝነት እንደሚሠራ በዚህ አጋጣሚ ያረጋግጥላችኋል፡፡ ከዚህ ትግል ጐን ለጐን የሁሉም ህዝቦች መሠረታዊ መብቶችና ጥቅሞች የሚከበሩባቸው ክልላዊና ሃገራዊ አጀንዳዎች በብቃት እንዲፈፀሙ በፅናት እንደሚታገልም ድርጅታችን በዚህ አጋጣሚ ቃል ይገባላችኋል፡፡

ድርጅታችን አዴፓ የአማራ ህዝብና ሁሉም የክልላችንና የሃገራችን ህዝቦች ከጐኑ ቆማችሁ አዚህ እንዲደርስ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ያለውን አድናቆት እየገለፀ አሁንም በክልላችንና በሃገራችን የተደቀኑ አደጋዎች እንዲቀለበሱና ከፊት ለፊታችን ያለውን ወርቃማ እድል አሟጠን እንድንጠቀም ዛሬም እንደወትሮአችሁ ከጐኑ በፅናት እንድትቆሙ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የመንግስትና የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች

አዴፓ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን በመራባቸው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ቀርፆ በስራ ላይ ያዋላቸውን የልማት ፕሮግራሞችና መርሃ ግብሮች ተቀብላችሁ በተሻለ ሙያዊ ብቃትና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ለመፈፀም ያደረጋችሁትን አኩሪ ርብርብ ከልብ ያደንቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔርተኝነት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ ለአማራ ብሔርተኝነት መጐልበት የመንግስትና የልማት ድርጅቶች ሠራተኞችም በተለያየ መልክ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጣችን አሁንም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው፡፡ በመንግስት ሠራተኞቻችን ዘንድ አሣሣቢ የሥራ ባህል መንሸራተት ይታያል፡፡ የአገልጋይነት መንፈስ ተዳክሟል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጣችን ውስጥ የሚታየው ሙስና ሙሉ በመሉ አልተስተካከለም፡፡ በመሆኑም በአዲስ ብሔራዊ የአርበኝነት መንፈስ ያደገውን የአማራ ብሔርተኝነት ለአስተማማኝ ልማትና ብልፅግና ማዋል እንዲቻል ከእነዚህ ችግሮች ፈጥነን በመውጣት ለቀጣይ ተልዕኮ እንድንዘጋጅ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የከተበራችሁ የክልላችን ምሁራንና ባለሃብቶች

የተያያዝነው የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አቅጣጫ የምሁራንንም ሆነ የባለሃብቱን ተሣትፎ ብቻ ሣይሆን የመሪነት ሚናቸውንም የሚሻ ነው፡፡ በልማት ረገድ ሃገራችን በቅድመ ካፒታሊስት የእድገት ደረጃ ላይ በመሆኗ አሁንም ከፍተኛ የገበያ ጉድለቶች አለብን፡፡ በመሆኑም የመንግስት ልማታዊ ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ ሊገደብ አይችልም፡፡ ያም ሆኖ ግን ድርጅታችን መንግስት በልማት ረገድ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት በግሉ ዘርፍ በማይሸፈኑ የስምሪት መስኮች ላይ ብቻ እንዲሆን ይሻል፡፡ ስለሆነም ለግሉ ዘርፍ መጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ትኩረት ይሰራል፡፡

ድርጅታችን ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ የመስራት ችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈታ መጥቷል፡፡ ከለውጥ በኋላ ደግሞ በድርጅታችን ሁለገብ እንቅስቃሴ ውስጥ የምሁራን ተሣትፎ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ በክልላችን፣ በሃገር አቀፍ ደረጃና በተለያዩ የዓለማችን ሃገራት የሚገኙ የአማራ ምሁራን በተለይም በመማክርታቸው አማካኝነት የለውጥ ሃሣቦችን በማመጨትና የተለያዩ አስተሳሰቦችን በማስተናገድ እየተጫወቱት ያሉት ሚና እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ ድርጅታችን የክልላችን ምሁራንና ባለሃብቶች እስካሁን ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ያለውን አድናቆት ይገልፃል፡፡ ቀጣይም በተጀመረው ከፍተኛ የመግባባትና የመቀራረብ መንፈስ አብራችሁት እንድትሰሩ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የከተበራችሁ የክልላችን ወጣቶች

እኛ የዛሬው የአዴፓ መሪዎች ነገን የምንተማመነው በእናንተ ላይ ባለን ተስፋ ነው፡፡ ክልላችንንም ሆነ ሃገራችንን እየፈተኑ ያሉት የሰላምና ደህንነት፣ የምርታማነትና የሥራ አጥነት ችግሮች ቀድመው የሚጐዱ እናንተን ነው፡፡ ከችግሮቹ የመውጫ ቁልፍ ያለውም በእናንተው እጅ ነው፡፡ በመሆኑም በክልላችን ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ፣ እድገታችን እንዲቀጥልና የሥራ አጥነት ችግር እንዲፈታ ትኩስ ጉልበትና እውቀታችሁን አስተባብራችሁ በአጭር ጊዜ እውን ከሚሆነው ከህብረ-ብሔራዊ ውህድ ፓርቲያችን ጐን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡

የከተበራችሁ የክልላችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች

ያለንበት መድረክ የአማራ ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ አንድ ሆኖ መቆም ያለበት ጊዜ ላይ ነው፡፡ የተለያዩ አላማዎችና ፕሮግራሞች ይዘን እየታገልን ቢሆንም በአንድ እንድንቆም የሚጋብዙን በርካታ አጀንዳዎች አሉን፡፡ ድርጅታችን በአሁኑ ወቅት በክልላችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ለተፈጠረው ትብብር ከፍተኛ አድናቆትና ክብር አለው፡፡ በሂደትም አንድ በሚያደርጉን አጀንዳዎች ዙሪያ የበለጠ ተናበንና ተቀራርበን እንድንሰራ በሚያለያዩን ጉዳዮች ላይ ደግሞ ተከባብረን እንድንታገል ይፈልጋል፡፡ አዴፓ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹም በዚሁ አቅጣጫ ለላቀ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንድትዘጋጁ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

- ሁለንተናዊ ብልፅግና ለሃገራችን!!! - ወቅታዊ ፈተናዎችን ወደ እድል ለመቀየር የሚያስችል አመራር እናረጋግጥ!!!

ድልና ድምቀት ለህዳር 11 39ኛው የአዴፓ የምስረታ በዓል! ዘለአላማዊ ክብር ለትግላችን ሰማዕታት! ህዳር 10/2012 ባህር ዳር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም