የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ምርጫ በሠላም ተጠናቀቀ

118

ኢዜአ፤ ህዳር 10/2012 የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ምርጫ በሠላም መጠናቀቁን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

አቶ ርስቱ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የሕዝበ ውሳኔው ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቁ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ አስመልክቶ ዛሬ ከማለዳው 12 ሠዓት ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ምርጫ በተቀመጠለት ሠዓት ተጠናቋል።

ምርጫው ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከዞኑ አስተዳርና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱን አንስተዋል።

"ሂደቱ በሠላማዊ ሁኔታ ተጠናቋል" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የክልሉና የፌዴራል ፀጥታ መዋቅር ከሰራው ስራ ባሻገር የሲዳማ ብሄር የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ለተጫወቱት ሚና ምስጋና ቸረዋል።

የሕዝበ ውሳኔ ውጤቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚገልጸው መሰረት ቀጣይ ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ቀጣይ ተግባራትን ሕዝቡ ተረጋግቶ  የሕዝቦችን አብሮናትና ወንድማማችነት በሚያጠናክር፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብት መንገድ ሠላማዊ እንዲሆንና ይኸው ቅንጅት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ክልሉን እየመራ ያለው ድርጅት ደኢህዴን የሕዝቡ ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመለስና ምርጫ እንዲካሄድ አቋም ወስዶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው በቅደመ ዝግጅትም የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ርስቱ ገለጻ ምርጫው ዴሞክራሲዊያዊ እንዲሆን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ገለጻ ሲደረግ ነበር፤ ይህም ውጤታማ እንዲሆን አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም