በመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰበት ነብር ሕክምና እየተደረገለት ነው

116
አክሱም (ኢዜአ) ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም---በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ታሕታይ ማይጨው ወረዳ "ማይ በራዝዮ" በተባለ አካባቢ መንገድ አቋርጦ ሲያልፍ በተሽከርካሪ ተገጭቶ ጉዳት የደረሰበት ነብር የህክምና እርዳታ እየተደረገለት ነው። በወረዳው የእንስሳት ክሊኒክ አስተባባሪ ዶክተር መድህን ግርማይ እንዳሉት በመኪና የተገጨው "ነብር" በጥንቅላቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በአሁኑ ወቅት ነብሩ ሕክምና እየተደረገለት መሆኑን የገለጹት ዶክትር መድህን፣ "ግሉኮስ እና የኢንፌክሽን መከላከያ መድኃኒት በመስጠት ክትትል እየተደረገለት ነው" ብለዋል። የነብሩን ሕይወት ለማትረፍ የተቻለውን ያህል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም ዶክተር መድህን አመልክተዋል። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ብርሃነ በበኩላቸው ነብሩ ዛሬ ጠዋት መገጨቱን በህብረተሰቡ መረጃው እንደደረሳቸው ለኢዜአ ተናግረዋል። መረጃ እንደደረሳቸው ወደ ተገጨበት አካባቢ በመሄድ የግጭቱ ሁኔታን ለማጣራት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። አቶ አበበ እንዳሉት የነብሩን  ሕይወት ለማትረፍ  በተሽከርካሪ ተጭኖ  ወደ ወረዳው የእንስሳት ክሊኒክ እንዲመጣ ተደርጓል። ነብሩን የገጨው ተሽከርካሪ ለጊዜው አለመያዙን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ አሽከርካሪዎች በሰው እና በእንስሳ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በኃላፊነት እንዲያሽከረክሩ አስገንዘበዋል። ነብሩ በተገጨበት አካባቢ ግራና ቀኝ በደን የተሸፈነ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አበበ፣ ነብሩ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላኛው አቋርጦ ለመሄድ ሲል ግጭት እንደደረሰበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም