በደንቢ ዶሎና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደት በሰላማዊ መንገድ እየተካሄደ ነው - የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች 

59

ኢዜአ፤ ህዳር 10/2012 በደንቢ ዶሎና በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ  የመማር  ማስተማር ሂደት በሰላማዊ  መንገድ እየተካሄደ መሆኑን የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዝዳንቶች ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎቹ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊነት ለማስቀጠል ከዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ፣ ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከአባገዳዎች ጋር በጥምረት እየሰሩ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት።

የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ለታ ተስፋዬ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርሲቲው ለሳምንታት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስታመር ሂደት መጀመሩን ገልጸው፤ በአሁኑ ጊዜም በዩኒቨርሲቲው የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና አባገዳዎች ካለፈው አርብ ጀምሮ ከተማሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ፤ ተማሪዎቹ ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንደሚያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱንም  ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።

ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የሄዱበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ፤ ማንም ከውጪ ሆኖ በማህበራዊ ሚዲያ በሚቀርጽላቸው እኩይ አጀንዳ መታለል እንደሌለባቸውም ፕሬዘዳንቱ መክረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም በተማሪዎች መመገቢያ፣ መኝታ ቤት እና ክሊኒክ አከባቢ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሉን የተናገሩት ዶክተር ለታ፤ ከተማሪዎች ጋር ተመሳስለው ገብተው ሁከት የሚፈጥሩ አካላት እንዳይኖሩም በዩኒቨርሲቲው መግቢያና መውጪያ በር ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው  የመማር  ማስተማር ሂደት የተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርቲው ተማሪዎች ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖትና ከብሔር ተጽዕኖ ነጻ ሆነው ትኩረታቸውን ለትምህርታቸው ብቻ እንዲሰጡ ለማድረግም የተለያዩ ውይይቶች መካሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችንም ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመሆን በመለየት እንዲስተካከል መደረጉንም ነው ዶክተር ጫላ የገለጹት፡፡

ሰሞኑን በሌሎች ዩኒቨርቲዎች የሚታዩ ችግሮች በዩኒቨርሲቲያቸው እንዳይከሰት  የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች ከተማሪዎች ጋር መምከራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት የስነ ምግባር ጥሰት  ፈጽመው  በተገኙ 88 ተማሪዎች፣ መምህራንና  የአስተዳደር  ሠራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱንም የዩኒቨርሲቲው  ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም