ባለሥልጣኑ ለጋዜጠኞች የሚሰጠው የአንድ ወር ስልጠና ነገ ይጀመራል

52
ኢዜአ ህዳር 10 / 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ከቻይና መንግስት ባገኘው ድጋፍ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ለተወጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ ። ከቻይና በመጡና ከፍተኛ ልምድ ባላቸው 12 ፕሮፌሰሮች በሚሰጠው ስልጠና 100 የመገናኛ ብዙሃን  ባለሙያዎች ይሳተፋሉ ብሏል። የባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ እንዳሉት ስልጠናው የክህሎት ማሳዳጊያ ነው። በሚዲያ ማኔጅመንትና በጋዜጠኝንት ዙሪያ የሚሰጠው ይህ ስልጠና ባለሙያዎቹ የተሻለ እውቅትና ልምድ የሚያካብቱበት እንደሚሆንም አክለዋል። የፕሮዳክሽን ስራና የሚዲያ ፍልስፍና ምን መምሰል አለበት፣ የመገናኛ ብዙሃን እንዴት መደራጀት አለባቸው እና ሌሎች በርካታ ሐሳቦች በስልጠናው ይካተታሉም ብለዋል። ስልጣው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተግባርና ኃላፊነታቸው በአግባቡ በመወጣት አገርና ሕዝብን በተገቢው መንገድ ማገልግል እንዲችሉ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የጎላ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ። በቀጣይም የሕዝብ ፍላጎትና የሚዲዎችን አቅም ማጎልበት የሚያስችል ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ከስልጠናው በኋላ የሚኖረውን ለውጥ በመዳሰስና ሚዲያዎች የሚያስተላልፏቸውን ፕሮግራሞች  በመቃኘት ጥናትና ትንተና ይሰራል ሲሉም አቶ ገብረጊዮርጊስ ተናግረዋል። በዚህም ጥንካሬና ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ ሙያ ነክ ስልጠናዎችን ለመስጠትና የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ የሚሰራ ይሆናል ነው ያሉት። ስልጠናው ከነገ ሕዳር 11 እስከ ታህሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ቅጥር ግቢ ይሰጣል ተብሏል።                                                                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም