የ ''ይቆጥቡ ይሸለሙ'' አፓርትመንት እድለኞች የቤት ቁልፍ ተረከቡ

104
ህዳር 10/2012  በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስምንተኛ ዙር የ''ይቆጥቡ ይሸለሙ'' የቤት ዕጣ የደረሳቸው ተሸላሚዎች የቤት ቁልፍ ርክክብ መርሃ ግብር ተከናውኗል። 1 ሺህ 595 የሽልማት ዓይነቶች በቀረቡበት የ8ኛው ዙር የ"ይቆጥቡ ይሸለሙ" የቆጣቢዎች የሽልማት መርሀ ግብር ዕጣ በሁለት ምድብ ሚያዝያ 24 እና ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ መውጣቱ ይታወሳል። በመርሃ ግብሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ አምስት አፓርትመንቶች፣ 30 ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ 30 ሞተር ሳይክሎች፣ 30 በጋዝና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ምድጃዎችና በርካታ ስማርት የሞባይል ቀፎዎች ለዕድለኞች ደርሰዋል፡፡ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ተሸላሚዎቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና እጅ የቤት ቁልፍ ተረክበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ''ይቆጥቡ ይሸለሙ'' ፕሮግራም የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማበረታታት ያለመ ነው። የሽልማቶችን አይነት በየጊዜው በማሻሻልና በቁጥርም በመጨመር አጓጊ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ባንኩ ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አገራዊ የቁጠባ ወር ማክበሩን ተናግረዋል። የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች እና ደንበኞች በተገኙበት ተሸላሚዎቹ የቤታቸውን ቁልፍ መረከብ ችለዋል። በጎንደር ዲስትሪክት የሚገኘውን የዳ ቅርንጫፍን ጨምሮ ከአምስት የተለያዩ ከተሞች ቅርንጫፎች የመጡ ተሸላሚዎች ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን ቁጠባ ከትንሽ ተጀምሮ እያደገ የሚሄድ መሆኑን ተናግረዋል። ከድሬዳዋ ዲስትሪክት ጀርሶ ቅርንጫፍ የአፓርታማ ቤት ዕድለኛ የሆኑት አቶ ታጁ ኡስማን ደስታቸውን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ቁጠባን ባህል ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ደንበኞች ማፍራት መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም