የሀገራችን የከተሞች ፎረም የጎረቤት አገራት ከተሞችን ለማካተት ታቅዷል

73
ኢዜአ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በሀገራችን በየዓመቱ የሚከበረው የከተሞች ፎረም የአጎራባች ሀገራት ከተሞችን ጭምር ለማሳተፍ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ገለጸ። ባለፈው ዓመት 8ኛው የከተሞች ፎረም በብቃት ያስተናገደችው የጅጅጋ ከተማ ለ9ኛው የከተሞች ፎረም አዘጋጅ አሶሳ ከተማ ልምዷን አካፍላለች ። በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀው የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መስፍን አሰፋ ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማ ልማት ቢሮ፣ የአሶሳ ከተማ ከንቲባ፣የሶማሌ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮና የጅግጅጋ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ ተገኝተዋል። ሚኒስትር ዴኤታው አቶ መስፍን አሰፋ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በጅግጅጋ ከተማ አዘጋጅነት የተከበረው የከተሞች ፎረም ከነበረው ያለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ፎረም ማዘጋጀቷ የሚደነቅ እንደነበር ገልፀዋል ። ሌሎች ከተሞች ለሁለት ዓመት ያክል ተዘጋጅተው ፎረሙን ሲያስተናግዱ ጅጅጋ ግን በአራት ወራት ውስጥ ብቻ የሚደነቅ በዓል ማስተናገዷን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው በፎረሙ ከሀገር ውስጥ 167 ከተሞች ከጎረቤት ደግሞ ጂቡቲ፣ ሀርጌሳና ገሮዊ ከተሞች መሳተፋቸውን አስታውሰዋል ። ይህንን ልምድ ለአሶሳ ከተማ በማካፈል የተሳካ ዝግጅት እንዲካሔድ መድረኩ አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል ። በፎረሙ ላይ ከተሳተፉ የውጪ ሀገር ከተሞች ከተገኘው ግብረ መልስ በመነሳት ቀጣይ በአሶሳ ከተማ በሚዘጋጃው ሀገር አቀፍ የከተሞች መድረክ ላይ የምስራቅ አፍሪካ ከተሞች እንዲሳተፉ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል ። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃሮን ዑመር በጅግጅጋ የከተሞች ፎረም ዝግጅት የታዩ  የኤግዚብሽን፣ የፀጥታ አከባበር፣ ህዝብን የማሳተፍና የፓናል ውይይት አዘገጃጀት ልምድ ከመድረኩ አግኝተናል ብለዋል ። ይህም በቀጣይ ክልላቸው ለሚያዘጋጀው መድረክ ጠቃሚ ልምድ እንደሚሆንላቸውን ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም