ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምታደርገው ድጋፍ ያስመሰግናታል ...የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞ ኮሚሽን

98
ሽሬእንዳስላሴ ሰኔ 13/2010 ኢትዮጵያ ለስደተኞች እያደረገች ላለው አቀባበል ምስጋና ሊቸራት እንደሚገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታወቀ። ዓለም ዓቀፍ የስድተኞች ቀን በትግራይ በአራቱ የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ካምፖች የተወከሉ ኤርትራውያን ስደተኞች  በተገኙበት ዛሬ  በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ በድምቀት ተከብሯል። በመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሽሬ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሚስተር ፋፋ ኦሊቨር አንቲዲዛ በእለቱ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃገራት ስደተኞችን ተቀብላ በሰላም እያኖረች ነው። “ለስደተኞቹ መጠለያ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ  መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩ በማድረጓ ምስጋና ሊቸራት ይገባል” ብለዋል። ስደተኞቹ  ሌሎች በርካታ እድሎች እንዲያገኙም ኢትዮጵያ ሙቹ ሁኔታ መፍጠሯን ገልጸው፤ የስድተኞችን ኑሮ ለማሻሻልም ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ድጋፍ እንዲያደርጉ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦም አድንቀዋል። የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የሰሜን ኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክኤ ገብረእየሱስ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ ለስደተኞች በሯን ክፍት አድርጋ ስደተኞችን  እየተቀበለች ያለች አገር ናት” ብለዋል። ኤርትራውያንን  ጨምሮ ከተለያዩ ሀገሮች  በኢትዮጵያ የተጠለሉ  ስደተኞች ከዘጠኝ መቶ ሽህ በላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበርም የስደተኞች ህይወት እንዲለወጥ የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች እንደምትገኝ ገልጸው በክልሉ ምእራባዊ ዞን የሚገኙት የስደተኛ ጣቢያዎች ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል። ስደተኞችን በመወከል ንግግር ያደረጉት  አቶ ቶፊቅ ኑርሁሴን እንዳሉት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከሚወዷት ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ቢሰደዱም መልካም ወንድማዊ አቀባበል እንደተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግም  በኤርትራ ስደተኞችና በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የእግር ኳስ ክለብ መካከል የውንድማማችነት የእግር ኳስ ጨዋታ አድርገዋል። እንዲሁም በኤርትራውያን ስደተኞች የተዘጋጁ የእደ ጥበብ ሥራዎችም በኢግዝብሽን መልክ ቀርበዋል። በምዕራባዊ ትግራይ ማይ አይኒ፣ ሽመልባ፣ ህፃፅና አዲ ሓሩሽ የስደተኛ ጣቢያዎች በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች ተጠልለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም