በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው

53
ሐረር (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2012ዓ.ም በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለምእሸት ተሾመ እንደገለጹት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት የተቋሙ የመማር ማስተማር ስራ ላለፉት 10 ቀናት ቀናት ተቋርጧል። የተቋረጠውን ትምህርት በነገው ዕለት ለማስጀመር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተከስተው በነበሩ ችግሮችና በመፍትሄዎቻቸው ላይ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ከጸጥታ አካላት፣ ከዩኒቨርሲቲው ቦርድ አባላትና ከአካባቢው መስተዳድር ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። በተጨማሪም የአካዳሚክ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮችንና የተማሪ ሕብረት አመራሮች በትምህርት አጀማመሩ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። እንደእሳቸው ገለጻ በትናንትናው እለትም በየትምህርት ክፍሉ የሚገኙ የተማሪ ተወካዮች እንዲወያዩ ተደርጓል። በዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎችን ከአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ወደ ተቋሙ የመመለስ ሥራ መከናወኑንና በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ መሆኑን ተናግረዋል። ከትናንት ምሽት ጀምሮ በሐረር ከተማ በሚገኙ የእምነት ተቋም ተጠልለው የሚገኙ ተማሪዎችን ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ወደዩኒቨርሲቲው ጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የማስገባት ሥራ በመካሄድ ላይ መሆኑንና ነገ ህዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም ትምህርት ለማስጀመር መታቀዱን አመልክተዋል። የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ሕብረት ሥራ አስፈጻሚ አባል ተማሪ ፍራንክሰን ጉደታ በበኩሉ በተቋሙ የተቋረጠውን ትምህርት በነገው እለት ለማስጀመር የተማሪዎች ሕብረት ካውንስል ከዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ጋር በትናንትናው ዕለት ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም