በትግራይ ምእራባዊ ዞን 5 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ስራ ተጀምሯል

135
ኢዜአ ህዳር 10/2012 ዓም  በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን 5 ሺህ 700 ሔክታር መሬት በመስኖ የማልማት ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ገለፀ ። በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ብርሃነ ተስፋይ ለኢዜአ እንደገለጹት የመስኖ ልማቱ 7ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮችን ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ዘንድሮ በመስኖ የሚለማው መሬት ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በአርሶ አደሮች ቁጥር በ1ሺህ 500 በመሬት ስፋት ደግሞ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ብለጫ እንዳለው ገልጸዋል። በበጋ ወራት ለማልማት ከታቀደው 5ሺህ 700 ሄክታር መሬት ውስጥ እስከ አሁን 2ሺህ100 ሄክታር መሬት በቲማቲም፣ሽንኩርት፣ጎመንና ሌሎች የጓሮ አትክልቶች ማልማት ተጀምሯል ። አርሶ አደሮቹ የተከዘ፣የባህረ ሰላምና የካዛ ወራጅ ወንዞችን በውሀ መሳቢያ ሞተር በመጠቀም ለመስኖ ልማት እንዲውል እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። የዘርፉ ምርታማነትን ለማሳደግም እስከ አሁን ድረስ ስድስት መቶ ኩንታል ማደበሪያና 43 ኩንታል ምርጥ ዘር በአርሶ አደሮች እጅ መድረሱን ገልጸዋል። ከዚሁ በተጨማሪ 51 የውሀ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች የተከፈፈለ መሆኑን ከቡድን መሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። በመስኖ ልማት  ስራ አዋጪና በኑሮአቸው ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በቃፍታ ሁመራ ወረዳ የባእከር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጠዓመ ቱኩእ ናቸው። አርሶ አደሩ እንዳሉት የጉድጓድ ውሀን በመጠቀም አራት ሄክታር መሬታቸውን በቲማቲም፣ሽንኩርትና ጎመን የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶች በማልማት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደር  ገብረጊዮርግስ ተስፋይ በበኩላቸው የተከዜ ውሀን በሞተር ፓምፕ በመሳብ ሶስት ሄክታር መሬት ፓፓያ፣ሙዝና ሌሎች አትክልቶች በማልማት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። የውሀ መሳቢያ ሞተር አቅርቦትና  የአርሶ አደሮች ፍላጎት ያለመጣጣም ክፍተት መኖሩንም አርሶ አደሩ ጠቁመዋል ። አርሶ አደሮቹ ለሚያከናውኑት የመስኖ ልማት ስራ የተጠናከረ የባለሞያዎች ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። በዞኑ ከመስኖ ልማት ስራው ከአንድ ሚልዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም