ድምፃችንን በሰላማዊ መንገድ ሰጥተናል - የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች

41
ኢዜአ፤ ህዳር 10/2012  ሰላማዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ድምፅ መስጠታቸውን በሲዳማ ክልል ህዝበ ውሳኔ የተሳተፉ የሀዋሳ ከተማ መራጮች ገለፁ። በከተማው ከሚገኙት ጣቢያዎች በሆገኔ ዋጮ ምርጫ ጣቢያ ላይ ድምፃቸውን የሰጡት አቶ ዳዊት ዮሐንስ  በሰጡት አስተያየት በህዝበ ውሳኔው ሂደት ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ገልፀዋል፡፡ አቶ ዳዊት ከሰልፍ ጀምሮ ድምፃቸውን በተዘጋጀው ኮሮጆ ውስጥ እንከሚያኖሩበት ድረስ ያሉ ሂደቶችን  በሠላማዊ መንገድ ማከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡ መንግስት ለህዝቡ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ባደረገው ጥረት መሠረት ህዝበ ውሳኔው በመከናወኑና  በሒደቱ ተሳታፊ መሆናቸው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ምርጫ ጣቢያ የተሳተፉት ወይዘሮ ትንሳኤ ከበደ በበኩላቸው ሁለት ወራት ያልሞላት ጨቅላ ልጃቸውን  ታቅፈው ድምፃቸውን ለመስጠት መምጣታቸውን ተናግረዋል ። የህዝበ ውሳኔውን ዕለት በጉጉት ሲጠባበቁት እንደነበር የተናገሩት ወይዘሮ ትንሳኤ እድሉ እንዳያመልጣቸው   ከአራስ ቤት ተነስተው ድምፅ መስጠታቸውን ገልፀዋል፡፡ የድምፅ አሰጣጡ ሂደት ሠላማዊ እንደሆነ መመልከታቸውን ገልፀው ለአካል ጉዳተኞች ፣ ነፍሰጡሮችና  አራሶች ቅድሚያ በመሠጠቱ ቶሎ መስተናገዳቸውን አስረድተዋል፡፡ በውቅሮ ሁለት ምርጫ ጣቢያ ድምፁን የሰጠው ወጣት ዳዊት አለማየሁ እንዳለው ደግሞ ህዝበ ውሳኔው ፍትሐዊና ሠላማዊ አካሄድን የተከተለ ነው ብሏል ፡፡ ከተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ ድምፁን መስጠቱንም ተናግሯል ፡፡ የህዝበ ውሳኔው ውጤት ምንም ይሁን ምን በበጎ መቀበል እንደሚገባ ያመለከተው ወጣት ዳዊት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሠላማዊ በመሆኑ መደሰቱን ነው አክሎ የገለጸው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም