የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መመቻቸቱ የህገ መንግስቱ ውጤት በመሆኑ እንዳስደሰታቸው የቀድሞ አመራሮች ገለጹ

75

ሀዋሳ ኢዜአ ህዳር 10/2012 የሲዳማ ህዝብ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መመቻቸቱ የህገ መንግስቱ ውጤት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው በደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የቀድሞ  አመራሮች ገለጹ።

አመራሮቹ ድምጽ ከሰጡ በኋላ እንዳሉት ዛሬ እየተካሄደ ያለው ህዝበ ውሳኔ የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት ሲያቀርብ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው ።

የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ በሰጡት አስተያየት “ለዛሬው የሲዳማ ክልልነት ህዝበ ውሳኔ ዕለት ደርሼ ማየት በመቻሌ የተሰማኝ ደስታ በቃላት የሚገለጽ አይደለም” ብለዋል።

ወላጅ አባታቸው ጭምር በቤተሰብ ደረጃም ለዚህ ሂደት ለመብቃት ብርቱ ትግል ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ህዝቡም ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረው ጥያቄ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር አብሮ በሰላም ለመኖር የሚችልበት ሁኔታ ጭምር እንዲፈጠር ተናግረዋል።

የህዝበ ውሳኔው ድምጥ አሰጣጥ ያለምን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ለዘመናት ያሳየውን ትዕግስት መቀጠል እንዳለበት አቶ ሚሊዮን አሳስበዋል።

የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ቃሬ ጫዊቻ በበኩላቸው ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የዘመናት ሲነሳ የነበረው የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መመቻቸቱ ትልቅ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የትግሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ህገመንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የዛሬው ህዝበ ውሳኔ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

“ለሲዳማ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ህዝቦች እንዲሁም በዓለም ደረጃ በልዩ ትኩረት የሚታይ ዕለት ነው፤ ፌዴራሊዝም በተግባር ዲሞክራሲያዊ በሆነ ነጻ ህዝብ ውሳኔና ይሁንታ እንዲያገኝ ለዚህ ቀን መብቃታችን እጅግ ልዩ ያደርገዋል” ብለዋል።

ዛሬ ህዝቡ በራሱ ጥያቄ ላይ የራሱን ምርጫ እንዲወስን እድል ያገኘበት ቀን በመሆኑ ለእሳቸው ልዩ እንደሚያደርገው የተናገሩት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ስኳሬ ሾዳ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ህልውና የተረጋገጠበት ፣ህገመንግስትና ፌዴራሊዝም አንድ ከፍታ ወደላይ ወጥተው የታዩበት ቀን ነው ብለው እንደሚወስዱት ገልጸዋል።

“የዚህ ሪፍረንደም ውጤት ምንም ይሁን ምን ህዝቡ በራሱ ጉዳይ ላይ ራሱ እንዲወስን ዕድል ያገኘበት ቀን ነው“ ብለዋል።

 “ህዝቡ በራሱ እንዲወስን የተደረገበት ቀን በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል” ብለዋል።

እየተካሄደ ባለው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት እስካሁን ባለው ሂደት ሰላማዊ ሆኖ  መቀጠሉን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ በመላው የሲዳማ ዞንና በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 1ሺህ 692 የምርጫ ጣቢያዎች እየተካሄደ እንደሚገኝ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም