በትግራይ 60 ሺህ ያህል ወጣቶችና ሴቶችን በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ለማሰማራት እየተሰራ ነው

57

መቐለ ኢዜአ ህዳር 10/12 በትግራይ ክልል በዘንድሮው ዓመት 60 ሺህ ወጣቶችና ሴቶችን በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ለማሰማራት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ወጣቶችና ሴቶቹ በበኩላቸው የሚሰጣቸውን ብድርና ያገኙትን የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠቅመው በሚሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል ።

በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የእንስሳት መኖና እርባታ ዳይሬክተር አቶ ተክላይ ገብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ያለውን የእንስሳት ሃብት ልማት ምርታማነትን ለማሳደግና በዘርፉ የወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

የታቀደውን ስራ ለማሳካት የወተት ሃብት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተሻለ ዝሪያ ያላቸው የአካባቢና የውጭ ላሞችን ተገዝተው ለወጣቶችና ሴቶች እንዲሰጡ የብድር አቅርቦት መመቻቸቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

ከእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ከፍተኛ የወተት ምርትን ጨምሮ 135 ሺህ ቶን ስጋ ፣ 72 ሺህ ኩንታል ማርና 28 ሺህ ኩንታል የዓሳ ምርት ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ዘንድሮ ከእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ከሚገኘው ምርት መካከል 70 በመቶ የሚሆነው ወደ ገበያ የሚቀርብ መሆኑንም  አቶ ተክላይ ገልፀዋል ።

በክልሉ ለእንስሳት ሃብት ልማት ምርታማነት ልዩ ትኩረት መሰጠቱ አርሶ አደሩን የተመጣጠነ ምግብ እንዲጠቀም ከማድረግ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዳው መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ዘንድሮ በክልሉ ከ41 ሺህ በላይ ወጣቶችና ከ17ሺህ በላይ ሴቶች ከዘርፉ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የሚሰማሩ ወጣቶች ስልጠና እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ የብድር አቅርቦቱ እየተመቻቸ መሆኑን አቶ ተክላይ ተናግረዋል።

ቢሮው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለወጣቶቹ ከሰጠው ስልጠናዎች ውስጥም በመኖ አቅርቦት፣የእንስሳት ዝሪያን መረጣና የመስሪያ ቦታዎች የመለየት ተግባራት ይገኙባቸዋል።

አርሶአደሩ ለእንስሳት ሃብት ልማት የሚሆን የተመጣጠነና በቂ መኖ የማቅረብ ልምዱ አነስተኛ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ 11 የተቀነባበረ የእንስሳት መኖ አቅራቢ ዩኒየኖች መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ተክላይ ይህም ለእንስሳት ምርታማነት መጎልበት ሚናው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በክልተ አውላዕሎ ወረዳ የ’’ማህበረወይኒ’’ ቀበሌ ነዋሪ የሆነውና በእንስሳት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ባለፈው አመት የተቀበለው ወጣት አብርሃ ግደይ እንዳለው በቅርቡ በእንስሳት ማድለብ የተሰጠው ስልጠና ሊሰማራበት ላሰበው ስራ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርለት ተናግሯል።

በቤተሰቦቹ ዋስትና እስከ 50 ሺህ ብር ለመበደር የሚያስችሉት ቅድመ ሁኔታዎች እያሟላ መሆኑን የተናገረው ወጣት አብርሃም በቀጣይነት ዘርፉን ለማሳደግ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት ፍላጎት እንዳለው  አስረድቷል።

በዶሮ እርባታ ዘርፍ ለመሰማራት ስልጠና መውሰዷን የገለጸችው ደግሞ በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን በእንደርታ ወረዳ ዓራቶ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው ወጣት አምለሰት ዓይናለም ናት።

በስልጠናው ላይ ስለተመጣጠነ የዶሮ ቀለብ አቀራረብ፣ለዶሮ የሚያስፈልገው እንክብካቤና የገበያ ሁኔታ አስመልክቶ በቂ ስልጠና በማግኘቷ ስራውን ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም