ዩኒቨርሲቲያችን ከሁከትና ብጥብጥ የፀዳ እንዲሆን ድርሻችንን እንወጣለን ... የአሶሳ ነዋሪዎች

213

ኢዜአ፤ሕዳር 10 / 2012  በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ግጭት ለማባባስ የሚደረገው ጥረት ለውጡን ለመቀልበስ ያለመ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ የአሶሳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ገለታ ጋጋ እንደሚሉት የለውጥ ሃይሉ የህዝቦችን ጥምረት በማጠናከር  በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይት ያለው ለውጥ እንዲመጣ ገንቢ ሚና ተጫውቷል፡፡

ለውጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስገኘውን ውጤት የሚጻረሩ አካላት ግጭት ለማባባስ በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ትኩረት አድረገው እየሠሩ በመሆናቸው ከመንግስት ጎን ቆመን ልናከሽፈው ይገባል ብለዋል ።

ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይረጋጉ የሚፈልጉ አካላት ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች እንደግጭት መቀስቀሻ መንገድ አድርገው እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት ደግሞ አቶ ኡመር አደም የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የመማር ማስተማር ግብዓቶችን አቅም በፈቀደ መጠን ማሟላትና ተማሪዎች ጥያቄ ሲያነሱ በአጭር ጊዜ መፍታት እንዳለበት መክረዋል፡፡

በዩኒቨርሰቲው ሠላም ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች በችግሩ ደግሞ ዋነኛ ተጎጂ  መሆናቸው የሚናገሩት ነዋሪዎቹ ተማሪዎች በየጊዜው በማወያየትና ችግሮች ሲከሰቱም ተማሪዎቹን እንደወላጅ በመንከባከብ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እንደሚሠሩ ገልፀዋል ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ)ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሐቅ አብዱልቃድር ሰሞኑን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰተው የጸጥታ ችግር በደረሰው የተማሪዎች ህልፈተ  ህይወት ልባችን ተነክቷል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች ድብቅ አደረጃጀት ዘርግተው ግጭት የሚያስነሱ በመኖራቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንኑ  ተረድቶ ችግሩን ለማስወገድ እንዲተባበር አስገንዝበዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ከማል አብዱራህማን ህዳር 03 ቀን 2012 ዓም በግቢው ጥቂት ተማሪዎች የምግብ አድማ በማድረግ ግጭት ለመቀስቀስ ሙከራ ማድረጋቸውን ገልፀዋል ።

ግጭቱን ለማባባስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 26 ተማሪዎች ተለይተው መታወቃቸውንና በመረጃ ላይ የተመሰረተ አስተማሪ ተግሳፅና ቅጣት እንደሚተላለፍ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴው በተረጋጋ መንገድ እንዲቀጥል የሃገር መከላከያ ሰራዊትና የፌደደራል ፖሊስ አባላት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከፖለቲካና ሃይማኖት ነጻ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አመልክተው ማንኛውም ግጭት የሚቀሰቅስ አካል በህግ እንደሚጠየቅ አስታውቀዋል፡፡

አንድ ተማሪ ከሚሞት ዩኒቨርሲቲው ቢዘጋ እንመርጣለን ያሉት ዶክተር ከማል ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ሁሉም የከተማው ማህበረሰብ በጋራ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም