በእሳት አደጋ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ

55
ኢዜአ ህዳር 10 /2012  በሆሳዕና ከተማ በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ አስታወቀ። የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ታምራት እሸቱ ለኢዜአ እንደገለጹት ትናንት ምሽት   3፡30 ላይ አደጋው የተከሰተው በከተማው አራዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ መናኽሪያ በተባለ አካባቢ ነው። የእሳት አደጋው መነሻ ለጊዜው ባይታወቅም ከመኪና እቃዎች መለዋወጫ ሱቅ እሳቱ እንደተነሳ አመላካች ክስተቶች መኖራቸውን ኢኒስፔክተሩ ጠቁመዋል። በእሳት ቃጠሎ አደጋው የመኪና እቃዎች መለዋወጫ ሱቁና ከጎኑ የነበሩ ሦስት የፑል ማጫወቻ ቤቶች መውደማቸውን ገልጸዋል፡፡ በእሳት አደጋው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የገለጹት ኢኒስፔክተር ታምራት እሳቱን ለማጥፋት ህብረተሰቡ ባደረገው ጥረት ወደ ሌላ ቦታ እንዳይዛመት ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ህብረተሰቡ አደጋውን ለመቆጣጠር ላደረገው ርብርብ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በቀጣይ ለእሳት አደጋ የሚያጋልጡ ነገሮችን በመለየት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም