የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሂደት ህጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥሪ ቀረበ

56
ኢዜአ ህዳር 9/2012 የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ሂደትና ውጤቱ ህጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥሪ አቀረቡ። እስካሁን በነበረው ሂደት መንግስትም ሆነ ህዝቡ ጥያቄው በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ ያደረጉት ጥረት የሚመሰገንና መቀጠል ያለበት መሆኑንም የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ለኢዜአ ተናግረዋል። የዩኒቨርስቲው የህግና አስተዳደር ኮሌጅ ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እንዳሉት፤ በህዝበ ውሳኔው ምርጫ ሂደት መንግስት፣ ህዝብ፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራንና ሌሎችም የማህበረሰቡ አካላት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ድረስ ህዝቡ በየጊዜው መረጃ እንዲያገኝና ግልፅ የሆነ አሰራር እንዲኖር ለማድረግ ጥሩ ስራ መስራቱንና በቀጣይም መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ሲካሄድ የመጀመሪያው እንደመሆኑ የህገ መንግስቱን ስልጣን በቀጥታ መሬት በማውረድና በተግባር ህዝበ ውሳኔው ለኢትዮጵያ ጥሩ ምሳሌ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል። በመሆኑም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እስከመጨረሻው ድረስ የህዝበ ውሳኔው ሂደት ስኬታማ እንዲሆን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በዩኒቨርሲቲው የፖሊሲና ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ታፈሰ ማቲዮስ በበኩላቸው ''ውጤቱ እስከሚገለፅ ድረስ ህዝቡ በሃሰተኛ መረጃ ሳይደናገር ቦርዱ የሚሰጠውን ትክክለኛ መረጃ በትዕግስት መጠበቅ አለበት'' ብለዋል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ሁሉም ዜጋ ተሳስቦና ተፈቃቅሮ እንዲሁም የውጭ ዜጎችም ካለ ስጋት የሚኖሩበት የኢትዮጰያዊነት መገለጫ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል ሲሉ ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም