የመንግስት ሰራተኛው ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ሰላም መስራት አለበት---የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር

55

ባህርዳር ኢዜአ ህዳር 09/2012፡- የመንግስት ሰራተኛው ከአፍራሽ ተልኮ እራሱን በማራቅ ለክልሉና ለሀገሪቱ ሰላምና ብልጽግና መስራት እንዳለበት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ላቀ አያሌው አሳሰቡ።

በባህር ዳር ከተማ  ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው  የመንግስት ሰራተኞች  ክልላዊ ውይይት ዛሬ ተጠናቋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት የመንግስት ሰራተኞች የተጣለባቸውን  የህዝብና የመንግስት አደራ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ሆኖም  አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች የህዝብን አገልግሎት እንዲያቀላጥፉ የተመቻቸላቸውን  ኮምፒውዩተርና ኢንተርኔት በመጠቀም አፍራሽ ተልኮን እንደሚያረመዱ አመልክተዋል።

የፖለቲከኞችና ግለሰቦችን ሃሳብ በመደግፍ የስራ ጊዜን ሲያባክኑ እንደሚውሉ ጠቅሰዋል።

"የህዝብን ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት መጀመሪያ ሰላም ያስፈልጋል "ያሉት አቶ ላቀ አሁን የሚስተዋለው የፖለቲከኞችና አጥፊ ግለሰቦችን ሃሳብ በማራገብ ጊዜን ማባከን ተገቢነት እንደሌላው አስረድተዋል።

"የአማራ ክልልን እርስ በርሱ በማጋጨት እና ውስጣዊ አንድነት እንዳይኖረው  የሚሰሩ አካላት እንዳሉ  ቢታወቅም ችግር የሚያባሱ ግለሰቦችን ህዝቡ አንድ ሆኖ ሊታገላቸው ይገባል " ሲሉ ገልጸዋል።

የክልሉ ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን  መጀመሪያ  የህግ የበላይነት መረጋጋጥ ይገባል።

የህግ የበላይነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚረጋገጠው ደግሞ የመንግስት ሰራተኛው ህግን ማክበር ሲችልና ህገ ወጥ ግለሰቦች ማስተማር ሲችል መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

አቶ ላቀ "የክልሉ መንግስት ህግ ለማስከበር  ቁርጠኛ አቋም ወስዶ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

የክልሉን ህዝብ በጎጥ በመከፋፈል ሰላሙ እንዳይረጋገጥና  እንዳይበለጽግ የሚያደርጉ አስተሳቦችን ለመመከትም የመንግስት ሰራተኛው በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመንግስት ሰራተኞች በበኩላቸው የሚሾመው  አመራር ለሚመራው ተቋም ብቁ እውቀት የሌለውና የሚመራውን ሰራተኛ በልጦ የሚገኝ ባለመሆኑ ለችግሩ መፈጠር መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ለሚያጋጥሙ ክፍተቶች በየደረጃው ያለ አመራር ችግር በመሆኑ  ክልሉን የሚመራው መንግስት የአመራሩን ቁመና ከላይ እስከታች መፈተሽሽ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ከባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የመጡት መምህርት  አብነት ባየ በሰጡት አስተያየት "  ክልሉን የሚመራው አዴፓ ህዝቡ ወደ ራሱ በመመልከት  ችግሮችን  በራሱ መፍታት እንዲችል በመስራት ላይ ውሱንነት አለበት "ብለዋል።

የመንግስት ሰራተኛው በአግባቡ ስራውን እንዲያከናውን ከተፈለገ የሚመራው በእውቀትና ክህሎት ከሱ የተሻለ ሆኖ መገኘት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

"የመንግስት ሰራተኛው ስራውን ከራሱ ፍላጎት ጋር አያይዞ ነው እያከናወነ ያለው "ያሉት ደግሞ ከዳንግላ ወረዳ ቴክኒክና ሙያ መምሪያ የመጡት አቶ ፋሲካ አዲስ ናቸው።

ህዝባዊ ወገንተኝነት ተሰምቶት የሚሰራ ሰራተኛ ውሱን መሆኑን አመልክተው የመንግስት ሰራተኛውን  የሚመራው አካል ስለሚመስል አመራሩ መስተካከል እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በውይይት መድረኩ ከአንድ ሺህ 500 በላይ የመንግስት ሰራተኞችና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም