በጎንደር የሰላም መደፍረስ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ታጥቷል

80
ኢዜአ  ህዳር 9/2012የጎንደር ከተማ ባለፈው ዓመት ተከስቶ በነበረው የሰላም መደፍረስ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቷን የከተማው ምክትል ከንቲባ ገለጹ፡፡ የከተማዋን ሰላም ዘላቂ በማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ተካሔዷል፡፡ ምክትል ከንቲባው ኢንጂነር በሪሁን ካሳው በውይይቱ ላይ ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍ እንዳመለከቱት በከተማዋ የተፈጠረው የሰላም እጦት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከግማሽ በታች ዝቅ አድርጎታል። ከዘርፉ 116 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር በመግለጽ፡፡ በዓመቱ ከተማውንና አካባቢው ይጎበኛሉ ተብሎ ከተጠበቁት 58 ሺህ የውጭ ቱሪስቶች መካከል  29 ሺህ  ብቻ መምጣታቸውን  ተናግረዋል። የከተማው የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴ በሰላም እጦት ጉዳት እንደደረሰበት አስረድተው በዚሀም በርካታ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄያቸውን የሰረዙበት አጋጣሚ እንደነበር አስረድተዋል ። ወጣቶች በአሁኑ ወቅት በከተማው የሰፈነውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል አደረጃጀቶችን እንዲያጠናክሩ ምከትል ከንቲባው አሳስበዋል። ሰላም ከሌለ ወጣቱ ሰርቶ መለወጥ እንደማይችልና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት እንዲያጠናከር የከተማው አስተዳደር ድጋፍ እንደያደርግላቸው የጠየቀው ደግሞ ወጣት ግዛቸው ወንድይፍራው ነው፡፡ ወጣት ማርቆስ ብሩ በበኩሉ በከተማው የተፈጠረው የሰላም እጦት የቱሪዝም፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በመጉዳቱ ወጣቶች ለሥራ አጥነት መዳረጋቸውን  ከውይይቱ መረዳቱን ገልጿል፡፡ የፀጥታ ሃይሉ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ለከተማው ሰላም መረጋገጥ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማድነቅ ወጣቱ አርአያነታቸውን ለመከተል ዝግጁ ነው ብሏል፡፡ በውይይቱ ላይ ከከተማው ስድስት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶችና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም